ቀጥታ፡

የንግድ ምክር ቤቶችና ማህበራት ለህዝብ ያላቸውን ተደራሽነት በመጠቀም ለምክክሩ አሳታፊነትና አካታችነት ሚናቸውን መወጣት አለባቸው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2018(ኢዜአ)፦ የንግድ ምክር ቤቶችና ማህበራት ለህዝብ ያላቸውን ተደራሽነት በመጠቀም ለሀገራዊ ምክክሩ አካታችነትና አሳታፊነት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር በመተባበር "በሀገራዊ ምክክር ሂደት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ" በሚል መሪ ሀሳብ በሀገራዊ ሰላምና መረጋጋት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ አዘጋጅቷል፡፡


 

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የግሉን ዘርፍ በመወከል ከመንግሥት ጋር ምክክር የሚያደርግ ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የብዝሀነትና የዕምቅ አቅም ባለቤት ብትሆንም ለዘመናት ከግጭት አዙሪት መውጣት አቅቷት ቆይታለች።

ስለሆነም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዜጎች ያልተግባቡባቸውን ዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች በምክክር መፍታት የሚችሉበትን አውድ መፍጠሩን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲወያዩና ለችግሮች የጋራ መፍትሔ ለመፈለግ የተቋቋመ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያውያን በነፃነት የሚነጋገሩበትን አውድ መፍጠር፣ የልዩነት መንስኤ የሆኑ አጀንዳዎችን መለየት እና በሂደቱ ላይ የሚወያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል፡፡

የምክክር ሂደቱ ከጅምሩ አካታችና ሁሉን አቀፍ መሆኑን ገልጸው፤ ነጋዴዎችና የንግድ ተቋማት ባለቤቶች ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ፌዴራል ድረስ በንቃት በመሳተፍ ሂደቱን ሲያሳልጡ ቆይተዋል ብለዋል፡፡

የንግድ ምክር ቤቶችና የንግዱ ማህበረሰብ ከተሳታፊነት ባለፈ በባለቤትነት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል፡፡

የንግድ ምክር ቤቶችና ማህበራት ለህዝብ ያላቸውን ተደራሽነት በመጠቀም ለሀገራዊ ምክክሩ አካታችነትና አሳታፊነት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡

የንግዱ ማህበረሰብ የሰላምን፣ የመቻቻል፣ የመግባባትና የአንድነት ትርክት በመፍጠር አምባሳደር መሆን ይችላል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ከህዝብ ጋር ባላቸው ቀረቤታ ተግባራዊ ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

የንግዱ ማህበረሰብ ለዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ ሚና እንዳለው በመጥቀስ፣ በቀጣይ በዋናው የምክክር ጉባኤ ላይ የህዝቡን ተሳትፎ በማጎልበትና የባለቤትነት ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ዓይናለም አባይነህ (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ አስተማማኝ ሰላም ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የጀመረው ሂደት በኢትዮጵያ ለንግዱ ማህበረሰብ ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት ምህዳር መፍጠር እንደሚያስችልም ገልጸዋል፡፡

የንግዱ ማህበረሰብ የግሉን ዘርፍ በመወከል ለምክክር ሂደቱ ስኬት የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ ገልጸው፤ ምክክሮች ወደ ተጨባጭ ውጤቶች እንዲቀየሩ የበኩላቸውን ተሳትፎ እንደሚያጠናክሩም አረጋግጠዋል።

የምክክር ኮሚሽኑ የጀመረው የምክክር ሂደት የጋራ እይታና የጋራ ልማት የሚያመጣ በመሆኑ ይህንኑ ጥረት በመደገፍ በንቃት እንደሚሳተፉ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት እና የአማራ ክልል ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች የቦርድ አባል እስማኤል አሊ፤ ችግሮችና አለመግባባቶች በውይይት ቢፈቱ የመጀመሪያው ተጠቃሚ የንግዱ ማህበረሰብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ንግድ ማህበረሰብ ከቀበሌ ጀምሮ አጀንዳዎቻቸውን እያስያዙ በንቃት ሲሳተፉ እንደነበር ገልጸው፤ መወያየትና መመካከር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቦጋለ ቢታኒ በበኩላቸው፤ የምክክር ሂደቱ በሰፊው የተሳተፉበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የምክክር ኮሚሽኑ ሥራዎች የላቁ መሆናቸውን ገልጸው፤ የሰላሙ ባለቤት የሆነው የንግዱ ማህበረሰብ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም