ኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ተቋማትን ለማጠናከር በቁርጠኝነት እየሠራች ነው - አምባሳደር ፀጋአብ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ተቋማትን ለማጠናከር በቁርጠኝነት እየሠራች ነው - አምባሳደር ፀጋአብ ከበደ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ተቋማትን ለማጠናከር እና ዘላቂ ሰላምን ማስፈን የሚያስችሉ መዋቅራዊ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን በጄኔቫ የተመድ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው ገለጹ።
62ኛው የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ከሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ እየተካሄደ ይገኛል።
በስብሰባው እየተካፈሉ የሚገኙት በጄኔቫ የተመድ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው የኢትዮጵያን ሀገራዊ መግለጫ (ሪፖርት) በስብሰባው ላይ አቅርበዋል።
መንግሥት የዲሞክራሲ ተቋማትን ለማጠናከርና በሀገር በቀል ፍላጎት ላይ የተመሰረተውን የሪፎርም አጀንዳ ለማስቀጠል እያከናወናቸው ያሉትን ውጤታማ ተግባራትን አንስተዋል።
አምባሳደሩ በቅርቡ የተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ተዓማኒና ሁሉን አካታች በሆነ መልኩ መካሄዱን ጠቅሰው ይህም የኢትዮጵያን ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ምኞትና ፍላጎት በተግባር ያሳየ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ምርጫው በስኬት መጠናቀቁ፣ የዲሞክራሲ ሥርዓቱን ለማጎልበትና ተቋማትን ለማጠናከር የተወሰደ ሌላው ትልቅ እርምጃ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
መንግሥት በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላምን ለማስፈንና በሀገር ባለቤትነት የሚመራውን የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ቀጣይነት ያለው ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አምባሳደር ፀጋአብ በሪፖርቱ ላይ አጽንኦት ሰጥተው አንስተዋል።
የሀገራዊ ምክክር ሂደት አሁን ላይ የመጨረሻውና ወሳኙ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ጠቅሰው፤ በመጪው ሐምሌ ወር 2018 ዓ.ም የምክክር ጉባኤ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።
ጉባኤው ሰፊ ሀገራዊ መግባባትን፣ ዕርቅ እና ዘላቂ ሰላምን ለመፍጠር ታሪካዊ ምዕራፍ እንደሚሆንም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ሪፖርት የሕግ የበላይነትን ይበልጥ ለማስከበር፣ የሲቪክ ምህዳሩን ለማስፋት እንዲሁም የሲቪል ማህበራት፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ባለድርሻ አካላት በዋና ዋና ሀገራዊ ሂደቶች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ እየተወሰዱ ያሉ መዋቅራዊ እርምጃዎችንም በስፋት አካቷል።
ኢትዮጵያ መርህን ለተከተለ ዓለም አቀፍ ትብብር ላይ ያላትን የጸና አቋምም አምባሳደሩ አንስተዋል።
ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ (OHCHR) ጋር ውይይት፣ ትብብር፣ የጋራ መከባበር እና ብሔራዊ ባለቤትነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ገንቢ ትብብር ለመፍጠር ያላትን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል።
በ62ኛው የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ አጀንዳዎች ላይ ኢትዮጵያ በንቃት እየተሳተፈች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ ለዜጎቿ ሁሉ የተመቸች ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊትና የበለጸገች ሀገር ለመገንባት የምታደርጋቸውን ጥረቶች አጠናክራ እንደምትቀጥልም በአጽንኦት አንስተዋል።
የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።