ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሕጋዊ የፍልሰት አስተዳደር ውጤታማነት ቀጣናዊና አህጉራዊ ትብብርን ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው

አዲስ አበባ፤ሰኔ 10/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሕጋዊ የፍልሰት አስተዳደር ውጤታማነት ቀጣናዊና አህጉራዊ ትብብርን ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከትምህርትና ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር 2ኛው ዓለም አቀፍ የፍልሰት ጉባኤ "የፍልሰትና አስገዳጅ ስደት ጥናት ለሰላምና ለዘላቂ ዕድገት በምሥራቅ አፍሪካና በአፍሪካ ቀንድ" በሚል መሪ ሃሳብ ውይይት ማካሄድ ጀምሯል።


 

በዚህ ወቅት የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ እንዳሉት፤ ሕጋዊ ስደት የኢንቨስትመንትና የዕውቀት ሽግግር በማስፋት ለሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ አለው።

በዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ ብሔራዊ ምክር ቤት በማቋቋም ስደትና ፍልሰትን በተቀናጀ ሥርዓት እየመራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በፍትሕ ሚኒስቴር የሚመራው የስደት አጋርነት ጥምረትን በመመስረት ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀልን የሚከላከል የሕግ ማዕቀፍ ተግባራዊ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የፍልሰት፣ስደተኞችና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢነት መመረጧም ቀጣናዊና አህጉራዊ ትብብርን ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።


 

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሹኔ በበኩላቸው፤ ሕጋዊነቱ የተጠበቀ ስደት የኢኮኖሚ ዕድገትን በማፋጠን ለባህልና ቀጣናዊ ትስስር ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም በሰው ሃብት ልማት፣ በጥናትና ምርምር ውጤታማነትን በማሳደግ ለማህበራዊ ፈጠራና ለውጥ መሰረት የሚጥሉ መፍትሔዎችን ማፍለቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል።


 

በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የስደት ጥናትና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ኢብራሂማ አማዱ፤ ስደትን በሕጋዊ ሥርዓት በማስተዳደር ለአፍሪካ ማህበራዊ ለውጥና የህዝብ ትስስር መጠቀም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ስደትና ፍልሰት አስተዳደር በተለያዩ ምክንያቶች የሚቀረጽ ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል ሕጋዊ፣ የፖሊሲ እና የተቋማዊ ማዕቀፎች፣ የሀገር ውስጥ፣ የቀጣናዊ እና የዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ ሁኔታዎች፣ የኃይል ፖለቲካ፣ የመንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት መኖር፣ እንዲሁም የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ፍላጎቶች ይገኙበታል።


 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንትን የወከሉት ፕሮፌሰር ፍቃዱ ጋሻው፤ ቀጣናዊና አህጉራዊ ትስስርን የሚያረጋግጡ በጥናትና ምርምር የተመሰረቱ መፍትሔዎችን እያፈለቀ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የምስራቅ አፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ የጉባኤው ተሳታፊዎች የስደትና ፍልሰት አስተዳደርን የሚያሻሽሉ ጥናቶችን ያቀርባሉ ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የስደትና ፍልሰት ጥናት ተቋም ኃላፊ አበባው ምናዬ(ዶ/ር) ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም