የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ ረቂቅ አዋጅ ታሳቢ ያደረገው የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባሻገር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ ረቂቅ አዋጅ ታሳቢ ያደረገው የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባሻገር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2018(ኢዜአ)፦የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ ረቂቅ አዋጅ ታሳቢ ያደረገው የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባሻገር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ነው ሲል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ ረቂቅ አዋጅ ላይ የሕዝብ እና የባለድርሻ አካላት ይፋዊ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሌ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ግብርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት፣ የኢንዱስትሪ ልማት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ዋነኛ መሠረት ነው።
ስለሆነም ኋላቀር ከሆነው የግብርና አሠራር በማላቀቅ ወደ ዘመናዊ፣ ተወዳዳሪ እና ገበያ መር ሥርዓት ማሻገር እንደሚገባ ገልጸዋል።
ይህ ረቂቅ አዋጅ ሲጸድቅ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች እና ከፊል አርሶ አደሮችን በኩባንያ በማደራጀት የመጠቀም መብታቸውን የሚያረጋግጥ ይሆናል ብለዋል።
እንዲሁም የእንስሳት ሀብታቸውን እና ጉልበታቸውን ወደ ካፒታል በመለወጥ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ የሚያስችል እንደሆነም ገልጸዋል።
የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ በዚሁ ወቅት፤ የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ማረጋገጥ የመንግሥት ዋና ትኩረት በመሆኑ ለዚህም በርካታ የፖሊሲ፣ የፕሮግራም እና የተቋም ሪፎርም ሥራዎች በሀገር ደረጃ እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
ይህ ረቂቅ አዋጅ ግብርናን ለማሸጋገር ከሚከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች መካከል ዋነኛው ሲሆን፤ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎችን እና ካምፓኒዎችን እንዲመሰርቱ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡
አርብቶ አደሩን በማደራጀት፣ የእንስሳት ዝርያዎችን በማሻሻል እና የጤና አጠባበቅን በማዘመን፣ አርብቶ አደሩ የራንች ባለቤት እንዲሆንና ሥራዎቹን በባለቤትነት እንዲያከናውን ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ ረቂቅ አዋጅ እንደሆነ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሤ እንደተናገሩት፤ ረቂቅ አዋጁ አርሶ አደሩን ወደ ኩባንያ አደረጃጀት በማሸጋገር የኢኮኖሚ እድገትን ይበልጥ ሊያፋጥኑ የሚችሉ አዳዲስ አቅሞችን መፍጠር ያስችላል ብለዋል።
ሂደቱ አርሶ አደሮች ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን በምጣኔ ሀብት ከመደገፍ ባለፈ፤ በሀገሪቷ የኢኮኖሚ መዋቅር ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ እንዲሆኑ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
በመጪዎቹ አምስት እና አስር ዓመታት ውስጥ አርሶ አደሮቹን ወደ ከፍተኛ ደረጃ በማሸጋገር ድንበር ተሻጋሪ የንግድ ሥራዎችን የሚያከናውኑና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ ትላልቅ የወጪ ንግድ ነጋዴዎች ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
በውይይቱ የተሳተፉት ባለድርሻ አካላት ረቂቅ አዋጁ እንደሀገር የተያዘውን የገጠር ትራንስፎርሜሽን ከግብ የሚያደርስ ነው ብለዋል።
አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተጠቃሚ እና አሳታፊ የሆነ ሥርዓት እንደሚዘረጋ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።