ቀጥታ፡

በጅማ ዞን በሌማት ትሩፋት የተሰማሩ ወጣቶች ውጤታማ እየሆኑ ነው

ጅማ፣ሰኔ 10/2018(ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን በሌማት ትሩፋት የተሰማሩ ወጣቶች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናገሩ።

የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ከተተገበረ ጀምሮ በጅማ ዞን በርካታ ዜጎች ተጠቃሚ መሆን መቻላቸው ተገልጿል።

መርሃ ግብሩ በተለይም ወጣቶች ከራስ አልፈው ለማህበረሰቡ የሚተርፍ ምርት እንዲያመርቱ ከማስቻሉም በላይ፣ የብዙዎችን የስራ አጥነት ችግር በዘላቂነት እየቀረፈ ይገኛል።

በዞኑ ጮራ ቦቶር ወረዳ ነዋሪ የሆነው ወጣት አሸናፊ ባጊዴ እና ጓደኞቹ ተደራጅተው በዶሮ እርባታ ስራ ላይ በመሰማራት ውጤታማ መሆን የቻሉ ወጣቶች ናቸው።

ወጣት አሸናፊ እንደሚያብራራው፣ ወጣቶቹ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ለረጅም ጊዜ ምንም አይነት የስራ እድል አላገኙም ነበር።


 

በመንግስት በተደረገላቸው ድጋፍ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ስር በዶሮ እርባታ የተሰማሩት እነዚህ ወጣቶች፤ በአሁኑ ወቅት በቀን ከሺህ በላይ እንቁላል ለገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ።

በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ በመጀመሪያው ዙር ብቻ ከ100 ሺህ ብር በላይ መቆጠብ መቻላቸውን ገልጸዋል።

ሌላኛው የዚሁ ወረዳ ነዋሪ የሆነው ወጣት አብዱላቂ አደም በሙዝ ልማት ላይ ተሰማርቶ ስኬታማ መሆን ችሏል።

የግብርና ባለሙያዎች ያቀረቡለትን የተሻሻለ የሙዝ ዝርያና ሙያዊ እገዛ በመጠቀም፣ ምርቱን በስፋት ለገበያ እያቀረበ መሆኑን ተናግሯል።

ከሚያገኘው ገቢ ራሱንና ቤተሰቡን ከመደገፍ ባለፈ፣ ለአራት የአካባቢው ወጣቶች ተጨማሪ የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ገልጿል።

በሊሙ ኮሳ ወረዳ በዘንድሮው አመት በከብት ማድለብ ስራ ላይ የተሰማሩት ወጣት ሁሴን አባዱራ እና ጓደኛውም በተመሳሳይ ውጤታማ እየሆኑ መሆናቸውን ይናገራሉ።

"ከዚህ ቀደም ምንም አይነት ስራ አልነበረንም፤ የከተማ አስተዳደሩ ባመቻቸልን የስራ እድል ተጠቅመን ወደ ስራ በመግባታችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ራሳችንን ችለን ለሌሎችም የስራ ዕድል መፍጠር ችለናል" ብለዋል።


 

የጅማ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቲጃኒ ተማም እንደገለጹት፤ በዞኑ በየአመቱ የሌማት ትሩፋት ተጠቃሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መጥቷል።

ዘርፉ ለበርካቶች የስራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ ማህበረሰቡ የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ እያገዘ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአሳ እና ከብት ዕርባታ፣ በንብ ማነብ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት እንዲሁም በዶሮ እርባታ የመርሃ ግብሩ ዋና ዋና ዘርፎች ናቸው ብለዋል።

በዞኑ በዘንድሮው አመት 314 ሺህ ሰዎችን የሌማት ትሩፋት ተሳታፊ ለማድረግ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ እቅዱን በማሻገር ከ339 ሺህ በላይ ዜጎችን የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የጽህፈት ቤት ኃላፊው ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም