በወላይታ ሶዶ ከተማ በህብረተሰብ ተሳትፎ የወባ መከላከል ሥራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በወላይታ ሶዶ ከተማ በህብረተሰብ ተሳትፎ የወባ መከላከል ሥራ እየተከናወነ ነው
ወላይታ ሶዶ፤ ሰኔ 10/2018 (ኢዜአ)፡-በወላይታ ሶዶ ከተማ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የወባ በሽታ መከላከል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የከተማው ጤና መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ፍሬው ዳዊት ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማው የክረምት ወራትን ተከትሎ የሚከሰተውን የወባ በሽታ ሥርጭት ለመከላከል ህብረተሰቡን በማሳተፍ እየተሰራ ነው።
በዚህም ከቤትና ከግቢ ጀምሮ ውሃ ያቆሩና ለወባ ትንኝ መራቢያ አመቺ የሆኑ ቦታዎችን የማዳፈንና የማፋሰስ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ቤት ለቤት በመሄድ የኬሚካል ርጭት ከማድረግ ባለፈ የአጎበር ስርጭትና የወባ በሽታ የታየባቸውን ሰዎች ፈጥኖ የማከም ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የወባ በሽታ ህብረተሰቡን እንዳይጎዳ ለቅድመ መከላከል ሥራ እና በሽታው ሲከሰትም አክሞ ለማዳን ልዩ ትኩረት መሰጠቱንም አቶ ፍሬው አመልክተዋል።
አስካሁን በተከናወኑ ተግባራት የተሻለ ውጤት መምጣቱን ገልጸው፤ በወባ በሽታ መከላከል ሥራው ህብረተሰቡ፣ የጤና ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል።
የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አማካኝነት እስከታች ወርዶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በከተማው የገነሜ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ አስቻለው ኢያሱ ናቸው።
በአጎበር አጠቃቀም፣ በአካባቢ ንጽህና እና በሽታን ቀድሞ በመከላከል ላይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በቅንጅት በተሰሩ ሥራዎች የወባ በሽታን የስርጭት መጠን ለመቀነስ እንደተቻለ ገልጸው፣ ወባን ቀድሞ የመከላከሉ ሥራ በንቅናቄ እየተመራ መሆኑን ተናግረዋል።
የወላይታ ሶዶ ከተማ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ተፈሪ ሐደሮ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በጤና ጣቢያው የወባ በሽታ ሥርጭት መከላከልና መቆጣጠር ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ነው።
በዚህም ህብረተሰቡን በማነቃነቅ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን ከማፋሰስና ከማዳፈን ባለፈ በአጎበር አጠቃቀምና በሕክምናው ላይ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።
ወደ ጤና ጣቢያው የሚመጡ ታካሚዎች በፍጥነት ሕክምና እንዲያገኙም አስፈላጊ ግብአቶችን የማሟላት ሥራ መከናወኑን ጠቁመዋል።
አቶ መስፍን መና እና ወይዘሮ መዝገቤ መስቀሌ የተባሉ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው እንዳሉት፣ የወባ በሽታ መከላከያ ዜዴዎችን በአግባቡ በመተግበር ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ከበሽታው እየተከላከሉ ነው።
በአካባቢያቸው የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታ እንዳይኖር የማጽዳትና ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን የማፋሰስ ሥራ በማከናውን ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለእዚህም ከጤና ባለሙያዎች ያገኙት ትምህርት በእጅጉ እንደጠቀማቸው ገልጸው፣ ወባን ቀድሞ መከላከል በሚቻልበት መንገድ ላይ ሌሎችንም በማስተማር እያስገነዙ መሆኑን ገልጸዋል።