ቀጥታ፡

በተንቀሳቃሽ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ፈጣንና ምቹ አገልግሎት አግኝተናል - ተገልጋዮች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ ተግባራዊ በተደረገው የተንቀሳቃሽ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰራር ፈጣን፣ ቀልጣፋና ምቹ አገልግሎት ማግኘት መቻላቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሚያዝያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ተንቀሳቃሽ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት በይፋ ተመርቆ ሥራ መጀመሩ ይታወቃል፡፡

ይህ ዘመናዊ አሠራር ነዋሪዎች ወደ ተለያዩ የመንግሥት ቢሮዎች መሄድ ሳይጠበቅባቸው፣ ባሉበት አካባቢ ሆነው ጉዳያቸውን በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ መፈጸም እንዲችሉ ምቹ ዕድል ፈጥሯል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች እንደገለጹት፤ አዲሱ የዲጂታል ተንቀሳቃሽ መሶብ አሠራር ቀደም ሲል የነበረውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችና እንግልቶች ያስቀረ ነው።

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል አቤል አለማየሁ እንደገለጸው የአገልግሎት የነዋሪነት መታወቂያውን በተንቀሳቃሽ መሶብ በ10 ደቂቃ ውስጥ ማሳደስ መቻሉን ተናግሯል።


 

ማንኛውንም አገልግሎት በአንድ ቦታ ማግኘት መቻሉ ጊዜን ለመቆጠብ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለውም አስታውቋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ መስፍን ተርፋ በበኩላቸው ቀደም ሲል መሰል ጉዳይ ለማስፈጸም ከሥራ ቀርተው ወደ ወረዳ ቢሮዎች በተደጋጋሚ ይመላለሱ እንደነበር አስታውሰዋል።


 

አሁን ግን በሻይ ዕረፍታቸው ወቅት በመምጣት በ5 ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጉዳያቸውን ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

የማዕከሉ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ባለሙያ ዳኜ መኮንን እንደተናገሩት፤ ከአስፈጻሚ ኤጀንሲዎች ጀምሮ እስከ ክፍለ ከተማና ወረዳ ያሉ መዋቅሮች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እርስ በእርስ በተናበበ ሁኔታ እየተሰራ ይገኛል።


 

መንገድ ፈንድና ፋይዳ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ባለሙያ እዝቹአለም ሲሳይ በበኩላቸው አሠራሩ ሕብረተሰቡ ሁሉንም አገልግሎቶች በአንድ ቦታ እንዲያገኝ የሚረዳ ነው ብለዋል።


 

አገልግሎቱ ተንቀሳቃሽ መሆኑ ደግሞ ነዋሪዎች እግረ መንገዳቸውን እንዲጠቀሙበት ዕድል በመፍጠሩ፣ በርካታ ተገልጋዮች በሥራው ተደስተውና አመስግነው እየሄዱ መሆኑን አስታውቀዋል።

ተንቀሳቃሽ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት አስተባባሪ ዳኛቸው ተፈራ፤ አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

አገልግሎቱ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ በከተማዋ በሚገኙ ሁሉም ክፍለ ከተሞች በመዘዋወር አገልግሎት መስጠቱን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም