የቢሾፍቱ ከተማ የኮሪደር ልማት የህብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ በተግባር ያዘመነና ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቢሾፍቱ ከተማ የኮሪደር ልማት የህብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ በተግባር ያዘመነና ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2018(ኢዜአ)፦ የቢሾፍቱ ከተማ የኮሪደር ልማት የህብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ በተግባር የቀየረና ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ገዛኸኝ ደጀኔ ገለጹ፡፡
ከተሞችን ምቹ የማድረግ፣ የማስዋብ እና የነዋሪዎችን ህይወት የማዘመን የኮሪደር ልማት መነሻ ከሆነችው አዲስ አበባ በቅርብ ርቀት የምትገኘው ቢሾፍቱ ፈለጓን በመከተል ላይ ትገኛለች።
የቢሾፍቱ ከተማ ምክትል ከንቲባ ገዛኸኝ ደጀኔ፤ ከተማዋን ለኑሮ ተመራጭ እና የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እቅድ ተይዞ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም በመጀመሪያው እና በሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት አንድ መቶ አስራ ሰባት ኪሎ ሜትር የአስፋልት፣ የብስክሌትና የእግረኛ መንገዶች መገንባታቸውን ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ የከተማዋ ስፍራዎች ስማርት ፖሎች መተከላቸውን፣ የደህንነት ካሜራዎች መገጠማቸውን አንስተው ልዩ ልዩ ፓርኮች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የኮሪደር ልማቱ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ፣ ቆሻሻን በአግባቡ እንዲያስወግዱና ለአረንጓዴ ልማት ትኩረት እንዲሰጡ የአስተሳሰብ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል።
ንጹህ አየር፣ የመዝናኛ ስፍራዎችና የተስተካከለ የትራፊክ ፍሰት በመፈጠሩ የነዋሪዎች አካላዊና አእምሯዊ ጤንነት እንዲጠበቅ ማገዙንም አመላክተዋል።
በኮሪደር ልማቱ 336 ሔክታር መሬት አረንጓዴ የማልበስ ስራ ተሰርቷል ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው፡፡
በከተማዋ የተዘረጋው ዘመናዊ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስመርን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶች የ24 ሰዓት የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር በማድረግ፤ የከተማዋን ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደጋቸውን ተናግረዋል።
ከተማዋ በገቢ ደረጃም በየዓመቱ 66 በመቶው እድገት እያስመዘገበች መምጣቷን ጠቁመው፤ ባለፉት አስራ አንድ ወራት ብቻ 14 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታውቀዋል።
በኮሪደር ልማቱና በሌሎችም ዘርፎች ለበርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች በሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን በማንሳት፥ እስካሁን ለ66 ሺህ ዜጎች በተለያዩ መስኮች ቋሚ የሥራ እድል ተፈጥሯል ብለዋል።
የኮሪደር ልማት የህብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ ያዘመኑና ተጠቃሚነትን ያረጋገጡ መሠረተ ልማቶችን እውን ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
በከተማዋ ሦስተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ተጠናክሮ መቀጠሉንም ምክትል ከንቲባው ጨምረው አስታውቀዋል።