ቀጥታ፡

በቀብሪ በያህ ከተማ በማህበር ተደራጅተው ሥራ የፈጠሩ ወጣቶች ውጤታማ ሆነዋል

ጅግጅጋ፤ ሰኔ 10/2018 (ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል ፋፈን ዞን ቀብሪ በያህ ከተማ በማህበር ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ ወጣቶች ውጤታማ መሆናቸውን አስታወቁ።

በሶማሌ ክልል ፋፈን ዞን ቀብሪ በያህ ከተማ፣ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ከሒልተን ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ዐውደ ርዕይና ባዛር በመካሄድ ላይ ነው።


 

በዚህ ለሁለት ቀናት በሚቆየው ዐውደ ርዕይና ባዛር ላይ 20 የተደራጁ ማህበራት ምርቶቻቸውን ለገበያ አቅርበዋል።

አብዲከሪን መሀመድ እና ጓደኞቹ በማህበር ተደራጅተው ከ500 በላይ  ዶሮዎችን በማርባት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሥራውን ከጀመሩ ወዲህ ራሳቸውን ከመቻል ባለፈ ለሌሎች ወገኖችም ድጋፍ ማድረግ መቻላቸውን ተናግረዋል።

ማኅበሩ ከአካባቢው ማኅበረሰብና ከስደተኞች የተውጣጡ አባላት በጋራ የመሠረቱት መሆኑን ገልጸው፤በማህበር ተደራጅተን ስራ ከጀመርን ወዲህ ህይወታችን መለወጥ ችለናል ብለዋል።


 

አብዲ አህመድኑር እና ጓደኞቹም በማህበር ተደራጅተው ለከተማዋ የአትክልት ምርቶችን በማቅረብ ረገድ ተጠቃሚ ከሆኑት ወጣቶች መካከል ናቸው።

በራሳቸው ከሚያመርቱት በተጨማሪም ከአምራች ገበሬዎችና ከአቅራቢዎች በመግዛት ለገበያ እንደሚያቀርቡ የገለጸው የማኅበሩ ሊቀመንበር ወጣት አብዲ አህመድኑር፤ ከሥራው ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁሟል።


 

ወጣቶች በመደራጀትና ሥራ በመፍጠር ራሳቸውን ከመቻል ባለፈ፣ ለሌሎች ወገኖችም ድጋፍ  መሆን እንደሚችሉ ገልፅዋል።

በዐውደ ርዕዩ የተገኙት የኢፌዴሪ የስደተኞች እና ተመላሽ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ብሩህተስፋ ሙሉጌታ እንደገለጹት፤ በቀብሪ በያህ ለሚገኙ ስደተኞች እና አስተናጋጅ ማህበረሰብ ማህበራዊና የኢኮኖሚ ትስስር  በመፍጠር የጋራ ተጠቃሚነትን የማጠናከር ስራ እየተሰራ ነው።


 

የዐውደ ርዕዩ ዓላማ የስደተኞችንና የአካባቢውን ማኅበረሰብ የገበያ ትስስርና የንግድ እንቅስቃሴ ማጠናከር ሲሆን፣ ይህም የማኅበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ውህደትና ራስን የመቻል ጥረቶችን እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

በዚህም ዐውደ ርዕዩ ስደተኞችንና የአካባቢውን ማኅበረሰብ በአካታች የኢኮኖሚ ዕድሎች የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም