ቀጥታ፡

በጋሞ ዞን ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል

አርባምንጭ፤ ሰኔ 10/2018 (ኢዜአ)፦ በጋሞ ዞን በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ቡድን መሪ አቶ ስንታየሁ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢንሼቲቭ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ልማት በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው።

በዞኑ ለዘንድሮው የክረምት ወራት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለፍራፍሬ፣ ለደን፣ ለጥምር ደን፣ ለእንስሳት መኖ የሚሆኑና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል ብለዋል፡፡

በዞኑ በማህበራት፣ በቡድን፣ በፕሮጀክት፣ በመንግስትና በግለሰብ ደረጃ የሚለሙ 397 ችግኝ ጣቢያዎች መኖራቸውን ጠቅሰው አስፈላጊው ችግኝ በበቂ ሁኔታ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በዚህም ከ24 ሺህ ሄክታር በላይ በሚሆን መሬት ላይ ተከላው እንደሚከናወን ጠቅሰው ለዚህም አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡

ለክረምቱ መደበኛና ለአንድ ጀምበር መርሃ-ግብሮች ስኬት የጉድጓድ ቁፋሮ ዝግጅት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መርደኪዮስ ኬርባ በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የሰው ልጅ ከእጽዋት ጋር ያለውን መስተጋብር በተጨባጭ ያሳደገ ነው ብለዋል።


 

በተጨማሪም የአየር ሚዛንን በማስተካከልና የአካባቢን ስነ ምህዳር በመጠበቅ ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና እያበረከተ መሆኑን ገልጸው በዘንድሮው ተከላም ህዝቡን በነቂስ ለማሳተፍ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም የችግኝ ዝግጅትና የጉድጓድ ቁፋሮ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ ልማት የሚያስገኘውን ጥቅም ህብረተሰቡ በአግባቡ እየተረዳ መምጣቱን የገለጹት ደግሞ በምዕራብ አባያ ወረዳ የኡጋዮ ቀበሌ አርሶ አደር ጀማል አንጃ ናቸው።


 

በተለይ እስካሁን በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ስራዎች የተጎዱ መሬቶች እያገገሙ፣ የደረቁ ምንጮች እየፈለቁና የሙቀት መጠን ሚዛኑ እየተስተካከለ መምጣቱን በተጨባጭ እያየን ነው ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ የሚተከሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች አካባቢን ከመጠበቅ ባለፈ ለምግብነትና ለኢኮኖሚ ምንጭነት እያገለገሉ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል። 

በየጊዜው በሚካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ሲሳተፉ መቆየታቸውን ጠቅሰው በዘንድሮው ዘመቻ ሙሉ ቤተሰባቸውን በማስተባበር ለችግኝ ተከላው መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም