ቀጥታ፡

ኮሌጁ የሌማት ትሩፋት ውጤታማነትን ለማጠናከር የበኩሉን እየተወጣ ነው

ሚዛን አማን፤ ሰኔ 10/2018 (ኢዜአ)፦ የሌማት ትሩፋት ውጤታማነትን ለማጠናከር የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን የሚዛን ግብርና፣ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ ገለጸ።

ኮሌጁ በሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ መሠረት እንቁላል፣ ወተት፣ ማር እና ዓሣ በብዛት አምርቶ ገቢውን ከማሳደግ ባለፈ ገበያን በማረጋጋት ማህበረሰቡን የማገልገል ግብ አስቀምጦ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አስታውቋል።

በኮሌጁ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ጥላሁን አለማየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ኮሌጁ ተማሪዎችን ከማሰልጠን በተጨማሪ ሀገራዊ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን መሠረት ያደረጉ የልማት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

ከዚህ ቀደም በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይ በስፋት ሲንቀሳቀስ እንደነበር አስታውሰው፣ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህም በሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ላይ ውጤታማ ሥራ ለመስራት አቅዶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በአሁን ወቅት በኮሌጁ ከ9 ሺህ በላይ እንቁላል ጣይ ዶሮዎች እንዳሉ ገልጸው፣ ከእነዚህም በቀን በአማካይ ከ5 ሺህ በላይ እንቁላል እንደሚሰበሰብ ገልጸዋል።

ይህም በከተማዋ የሚስተዋለውን የእንቁላል እጥረት ችግር በተወሰነ መንገድ መፍታቱን ገልጸው፣ በወተት ምርትም ተመሳሳይ ውጤት ለማስመዝገብ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለእዚህም ከ50 በላይ ላሞችን መያዝ የሚችል ግንባታ እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጥላሁን፣ በተመሳሳይ የሥጋ ዶሮ ለማርባት የሚያስችል ሼድም እየተዘጋጀ ነው ብለዋል።

ከ300 በላይ የንብ ቀፎዎችን በማዘጋጀት የንብ ማነብ እና የዓሣ እርባታ ተግባራትም በዚህ ዓመት በኮሌጁ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ መሆኑን አቶ ጥላሁን አክለዋል።

እንደ እሳቸው ገለጻ ኮሌጁ ምርት ከማምረት ባሻገር የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች በማቅረብ ውጤታማ እንዲሆኑ እያገዘ ነው።

በኮሌጁ የወተት እርባታ ፕሮጀክት ላይ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል ወጣት ታምራት አስራት እና መዓዛ ጥላሁን በገቢም በምርትም ተጠቃሚ እየሆንን ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት 15 የወተት ላሞችን በመንከባከብ፣ ወተት በማለብና ለሽያጭ በማዘጋጀት ሥራ በሚያገኙት ገቢ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን እያስተዳደሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሌላው የምርቱ ተጠቃሚ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪ አቶ እሰይ ኮንታ የሌማት ትሩፋት ሥራ በከተማዋ ከፍተኛ የእንቁላል ምርት እንዲኖር ማስቻሉን ገልጸው፣ ለዚህም ኮሌጁ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል ብለዋል።

ለከተማው ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበ ያለውን የኮሌጁን የእንቁላልና የወተት ምርት ወስደው ልጆቻቸውን በመመገብ ጤናማና የተስተካከለ ዕድገት እንዲኖራቸው እያደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም