የንግዱ ማህበረሰብ በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ባለቤት እና አሳላጭ መሆን ይጠበቅበታል - ኢዜአ አማርኛ
የንግዱ ማህበረሰብ በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ባለቤት እና አሳላጭ መሆን ይጠበቅበታል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2018 (ኢዜአ)፦ የንግዱ ማህበረሰብ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ላይ ንቁ ተሳታፊ፣ ባለቤት እና የሂደቱ አሳለጭ በመሆን ለስኬቱ የበኩሉን ሚና አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር በመተባበር "በሀገራዊ ምክክር ሂደት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ" በሚል መሪ ሀሳብ በሀገራዊ ሰላምና መረጋጋት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ አዘጋጅቷል።
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የግሉን ዘርፍ በመወከል ከመንግስት ጋር ምክክር የሚያደርግ ተቋም ነው።
ኮሚሽነር አምባዬ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የብዝሀነት የዕምቅ አቅም ባለቤት ብትሆንም ለዘመናት ከግጭት አዙሪት መውጣት አቅቷት ቆይታለች።
ስለሆነም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዜጎች ያልተግባቡባቸውን ዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች በምክክር መፍታት የሚችሉበትን አውድ መፍጠሩን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲወያዩና ለችግሮች የጋራ መፍትሔ ለመፈለግ የተቋቋመ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያውያን በነፃነት የሚነጋገሩበትን አውድ መፍጠር፣ የልዩነት መንስኤ የሆኑ አጀንዳዎችን መለየት እና በሂደቱ ላይ የሚወያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የመለየት ብሎም ሌሎች ውጤታማ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
የምክክር ሂደቱ አካታችና ሁሉን አቀፍ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ነጋዴዎችና የንግድ ተቋማት ባለቤቶች ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ፌዴራል ድረስ በሂደቱ ላይ ንቁ ተሳታፊና አሳላጭ በመሆን ገንቢ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።
የንግዱ ማህበረሰብ ለዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ ሚና እንዳለው በመጥቀስ፣ በቀጣይ በዋናው የምክክር ጉባኤ ላይ የህዝቡን ተሳትፎ በማጎልበትና ባለቤትነት ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትም ይህንን ሚናውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ዓይናለም አባይነህ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የጀመረው ሂደት ለኢትዮጵያ የንግዱ ማህበረሰብ ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት ምህዳር ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።
የንግዱ ማህበረሰብ የግሉን ዘርፍ በመወከል ለምክክር ሂደቱ ስኬት የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ ገልጸው፤ ምክክሮች ወደ ተጨባጭ ውጤቶች እንዲቀየሩ የበኩላቸውን ተሳትፎ እንደሚያጠናክሩም አረጋግጠዋል።
ምክር ቤቱ ለኮሚሽኑ አስፈላጊውን የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግ በመጥቀስ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እንደሚወጣም አረጋግጠዋል፡፡