የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ለመንግሥት ግዥ ሥርዓት ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ለመንግሥት ግዥ ሥርዓት ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2018 (ኢዜአ)፦ የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ለመንግሥት ግዥ ሥርዓት ውጤታማነት፣ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ የፌዴራል ንብረትና ግዥ ባለስልጣን አስታወቀ።
በበጀት ዓመቱ ባለፉት 11 ወራት ከ370 ቢሊዮን ብር በላይ በኤሌክትሮኒክ የግዥ ስርዓት መፈፀሙም ተጠቅሷል።
የፌዴራል ንብረትና ግዥ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሰረት መስቀሌ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለፉት 11 ወራት የቁጥጥር ሥርዓቱን ለማጠናከርና የተቋማትን አቅም ለማጎልበት የአሰራር ሥርዓቶችን በማዘመን ረገድ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።
በአስተዳደር ስርዓቱ ውስጥ የአዋጅ መሻሻል እንዲሁም የመመርያዎቹ መውጣት ተከትሎ መዘጋጀት ያለባቸው መደበኛ የጨረታ ሰነዶችና ማንዋሎችን እንዲሁም የአሰራር ስርዓቶችን በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።
በዚህም 41 የሚሆኑ መደበኛ የጨረታ ሰነዶች በማዘጋጀት ለተጠቃሚዎች ተደራሽ የተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ 32ቱ የፌዴራል የመንግስት ግዥና ንብረት ሽያጭ የሚፈፀምባቸው መደበኛ የጨረታ ሰነዶች ሲስተም ውስጥ ተካተው ስራ ላይ ማዋል ተችሏል ብለዋል።
በ2017 እና 2018 ሁሉም ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ግዥያቸውን የፈጸሙት በእቅዳቸው መሰረት እንደሆነ ገልፀው አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በየሩብ አመቱ እቅዳቸውን ማሻሻል የሚያስችል አማራጭ እንዳለው አንስተዋል።
በበጀት ዓመቱ 367 የፌዴራል ባለበጀት መስሪያቤቶች ግዥያቸውን በኦንላይን እየፈፀሙ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ 11 ወራት ውስጥ ከ29 ሺህ በላይ ጨረታዎች ተካሂደው ከ370 ቢሊዮን ብር በላይ በኤሌክትሮኒክ ሥርዓት የተፈጸመ ሲሆን፣ ይህም ያልታቀደ ግዥን በማስቀረት የሕዝብና የመንግሥትን ሀብት ከብክነት ለመጠበቅ ትልቅ እገዛ አድርጓል ብለዋል።
የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓት የተገልጋዮችን የጊዜ ብክነትና አላስፈላጊ የትራንስፖርት ወጪን በማስቀረት፣ ባሉበት ቦታ ሆነው የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሏልም ብለዋል።
ይህ አሰራር ከሰዎች ንክኪ ነፃ በመሆኑ ለአቅራቢዎች፣ ለተወዳዳሪዎችና ለግዢ ፈጻሚ መስሪያ ቤቶች የጎላ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን አስገንዝበዋል።
መረጃን በቀላሉ ለሁሉም ተደራሽ የሚያደርግ መሆኑም ተጠያቂነትን በማስፈን ብልሹ አሰራርን በከፍተኛ ደረጃ ለመከላከል የሚያስችል ነው።
የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ለመንግሥት ግዥ ሥርዓት ውጤታማነት፣ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን አብራርተዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስራዎችን በማጠናከር ተጠቃሚዎችን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስኬትም ሥርዓቱን በክልሎች የማስጀመር ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።