ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ እየተጫወተች ያለው የመሪነት ሚና በአስተማማኝ መሠረት ላይ እየተገነባ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ እየተጫወተች ያለው የመሪነት ሚና በአስተማማኝ መሠረት ላይ እየተገነባ መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን ገለጹ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር በቂሊንጦ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ያስገነባውን ግዙፍ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ መሙያ ጣቢያ አስመርቋል፡፡


 

የትራንስፓርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ መሙያ ጣቢያዎችን በማስፋፋት ላይ ትገኛለች፡፡

በአሁኑ ወቅት በርካታ ፈጣን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ መሙያ ጣቢያዎች በስፋት እየተገነቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይህም አገሪቱ በዘርፉ ላይ እየተጫወተች ያለው የመሪነት ሚና በአስተማማኝ መሠረት ላይ እየተገነባ ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተግባራዊ ምላሽ እየሰጠች መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የዚህ ግዙፍ የቻርጅ መሙያ ጣቢያ እውን እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ በቀጣይም በዘርፉ ለሚከናወኑ ስራዎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም