ቀጥታ፡

በምስራቅ ቦረና ዞን የስንዴ ልማትን በማስፋፋት የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል

ነገሌ፤ ሰኔ 10/2018 (ኢዜአ)፦በምስራቅ ቦረና ዞን በበልግ አዝመራ የስንዴ ልማትን በማስፋፋት የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ሊበን ቦሩ፤ በዞኑ በልግ አዝመራ 176 ሺህ 223 ሄክታር መሬት በስንዴ፣ ጤፍ፣ ቦለቄ እና ቦቆሎ መልማቱንም አስታውቀዋል፡፡

ከዚህም ውስጥ 61 ሺህ 643 ሄክታር  መሬት  በስንዴ ልማት በመሸፈን የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በስንዴ ልማቱ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግም የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን ከመተግበር ባለፈ ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ  በወቅቱ ለአርሶ አደሩ  እንዲቀርብ ተደርጓል ብለዋል።

በዞኑ በስንዴ ልማት ከተሸፈነው መሬት  አብዛኛው በኩታ ገጠም የለማና በመስመር የተዘራ በመሆኑ ሰብሉ በአሁኑ ወቅት በጥሩ ቁመና ላይ ይገኛል ብለዋል።

በዞኑ ከ42ሺህ 130 በላይ አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮችን በማሳተፍ በስንዴ ከለማው ማሳ 1 ሚሊዮን 365 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል፡፡

በዞኑ አርሶ አደሮች እና ከፊል አርብቶ አደሮችን ከእርዳታ ጠባቂነት ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር የግብርና አሰራርን ለማዘመን እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ የባለሙያ ድጋፍም መደረጉንም ገልጸዋል።

በበልግ እርሻ ከተሳተፉ አርሶ አደሮች መካከል በዞኑ ሊበን ወረዳ የጎቢቻ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አብዲ ኑር እንዳሉት የተሻሻለ የግብርና አሰራርን በመጠቀም በሦስት ሄክታር መሬታቸውን ላይ ስንዴ አልምተዋል።


 

በስንዴ  ልማቱን ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ መከተላቸውና የተስተካከለ የዝናብ ስርጭት መኖሩ ስራቸውን ውጤታማ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡

ወረዳው ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ እንዲሁም ትራክተር በወቅቱ ማቅረቡ ስራቸውን በተገቢው ለማከናወን እንዳስቻላቸውም ጠቁመዋል።

የእዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ወርቁ አለባቸው በበልግ ወቅት በስንዴ ካለሙት ሦስት ሄክታር መሬት የተሻለ ምርት እንደሚያገኙ ተስፋ ማድርጋቸውን ተናግረዋል።


 

በግብርና ባለሙያ ድጋፍ ታግዘው ያከናወኑት የስንዴ ልማት በጥሩ ሁኔታ ላይ መገኘቱ የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል። 

በምስራቅ ቦረና ዞን ከመጋቢት አጋማሽ እስከ ሚያዚያ የዝናብና የዘር ወቅት ሲሆን ከሐምሌ አጋማሽ እስከ ነሀሴ የምርት መሰብሰቢያ ወቅት መሆኑን ከዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያሳያል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም