አርሶ አደሮች ከሰብል ልማት በተጓዳኝ ቀይ ሽንኩርት በማምረት ተጠቃሚ ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
አርሶ አደሮች ከሰብል ልማት በተጓዳኝ ቀይ ሽንኩርት በማምረት ተጠቃሚ ሆነዋል
ጭሮ ፤ ሰኔ 10/2018 (ኢዜአ)፦ከሰብል ልማት በተጓዳኝ በቀይ ሽንኩርት ማምረት ላይ በመሰማራት ተጠቃሚ መሆናቸውን የምዕራብ ሐረርጌ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ።
በዞኑ ከ26 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በበልግ እርሻ ቀይ ሽንኩርትን በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጸው ደግሞ የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ፅህፈት ቤት ነው።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የገመቺስ ወረዳ አርሶ አደሮች እንደገለጹት፤ በመደበኛው የበልግ አዝመራ በዋናነት ከሚያለሙት የእህል ሰብል በተጓዳኝ ቀይ ሽንኩርት በማልማት ከፍተኛ ገቢ እያገኙ ነው።
በወረዳው ቁኒ ሶገሪያ ቀበሌ አርሶ አደር አብዮት ሽመልስ ፤ ቀደም ሲል በበልግ እርሻ የምግብ ሰብል ምርት ላይ ብቻ ተወስነው የቆዩ ቢሆንም አሁን ላይ ሽንኩርት ማምረታቸውን ገልጸዋል።
ባለፈው መኸር ግማሽ ሄክታር በሚጠጋ ማሳ ላይ ያለሙትን 50 ኩንታል ሽንኩርት ለገበያ በማቅረብ ከ280 ሺህ ብር በላይ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከዘርፉ እያገኙ ባለው ገቢም ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በበቂ መጠን ገዝተው ከመጠቀም ባለፈ ጥሪት ለማፍራት መቻላቸውን አስረድተዋል።
በተያዘው የመኸር ወቅት እርሻም ከሌሎች ሰብሎች ጋር በጥምር ልማቱን በማስፋፋት ላይ መሆናቸውን የተናገሩት አርሶ አደሩ እስከ 80 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁም ገልፀዋል።
ሌላኛው አርሶ አደር ፀጋዬ ታረቀኝ በበኩላቸው፤ የሽንኩርት ምርት ገበያ ላይ ተፈላጊ ከመሆኑም ባለፈ ነጋዴዎች አካባቢያቸው ድረስ መጥተው ምርታቸውን ስለሚረከቡ የስራ ተነሳሽነታቸው መጨመሩን ተናግረዋል።
ከልማቱ በሚያገኙት ገቢ የሰብል ልማታቸውን ከማስፋፋት ባለፈ የቀንድ ከብት ገዝተው በማድለብ ገቢያቸውን ለማሳደግ አቅም እንደፈጠረላቸው አስረድተዋል።
ባለፈው በልግ ወቅት 35 ኩንታል ምርት ለገበያ በማቅረብ ከ170 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት ምርጥ ዘርና ማዳበሪያን በመጠቀም ምርታማነታቸውን ለማሳደግ በትኩረት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የምዕራብ ሐረርጌ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ፅህፈት ቤት የሰብል ልማት አስተባባሪ አቶ መደቅሳ ዴሬሳ ፤በዞኑ 15 ወረዳዎች በበልግ አዝመራ 5 ሺህ 535 ሄክታር የሚሆን መሬት በቀይ ሽንኩርት መልማቱን ገልፀዋል።
በልማቱም ከ26 ሺህ 270 በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ መሆኑን ጠቅሰው ውጤታማ እንዲሆኑ በግብርና ባለሙያዎች የቅርብ ድጋፍና እገዛ እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ለልማቱ ስኬታማነት 2 ሺህ 212 ኩንታል ማዳበሪያ እና 144 ኩንታል የሽንኩርት ምርጥ ዘር መቅረቡን ጠቁመዋል።
በዞኑ እየተካሄደ ባለው የሽንኩርት ልማት ከ770 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል።