ዩኒቨርሲቲው ምርታማነትን ለማላቅ የሚያስችሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው ምርታማነትን ለማላቅ የሚያስችሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ እያደረገ ነው
አዳማ ፤ ሰኔ 10/2018 (ኢዜአ)፦የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ምርታማነትን ለማላቅ የሚያስችሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ በማድረግ ለማህበረሰብ ተጠቃሚነት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገለፀ።
የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፍቃዱ ምትኩ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው ምርታማነትን ለማላቅ የሚያስችሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ በማድረግ ለማህበረሰብ ተጠቃሚነት እየሰራ ነው።
ዩኒቨርሲቲው በተለይ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብርን ለማሳካት የሚያስችሉ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትን ለአርሶ አደሩ የማድረስ ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም ለስራ አጥ ወጣቶችና ለአርሶ አደሩ የእርባታ ዶሮዎችን በማከፋፈል ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው በራሱ አቅም ጫጩቶችን በማስፈልፈል ለህብረተሰቡ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ከ3 ሺህ በላይ ዶሮዎችን በማስገባት ወደ 40 ሺህ የሚጠጉ እንቁላሎችን ለገበያ እያቀረበ መሆኑን አስረድተዋል።
የተሻሻሉ የወተት ላም ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ የተሻለ ሆርሞን ያላቸውን የኮርማ ዝሪያዎች በሰው ሰራሽ ስነ-ዘዴ በማዳቀል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
በዚህም የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያን በማቋቋም የተሻለ ስራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በሌላም በኩል ሶስት የተሻለ ምርት መስጠት የሚችሉ የስንዴ፣ የጤፍና የአጃ ሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረጉን ገልጸዋል።
በዚህም ረገድ ከ1 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ መደረጉን የገለፁት ፕሬዚዳንቱ በአሁኑ ወቅት በበጋ መስኖ በ12 ሄክታር መሬት ላይ የለማ የስንዴ ምርጥ ዘር ምርት እየተሰበሰበ ይገኛል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው የግብርና ልማት ስትራቴጂን ለመደገፍ እያከናወነ ከሚገኘው ተግባር ባሻገር ጤናማ ማህበረሰብን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ እየሰራ እንደሚገኝም አክለዋል።