በኦሮሚያ ክልል በበጀት ዓመቱ የተመረተ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ እየቀረበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል በበጀት ዓመቱ የተመረተ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ እየቀረበ ነው
አዳማ፤ ሰኔ 10/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በበጀት ዓመቱ የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ በተደረገ እንቅስቃሴ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቶን ቡና ተመርቶ ለማዕከላዊ ገበያ እየቀረበ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የቡናና ፍራፍሬ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መሀመድ ሳኒ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ የቡና ልማት ለአርሶ አደሩ የኢኮኖሚ ምንጭነት ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።
ይህንን አጠናክሮ ለማስቀጠል የቡና ማሳን በማሳደግ ልማቱን ከማስፋፋት ባለፈ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የተሻሻሉ ግብዓቶችና የተፈጥሮ ማዳበሪያ በአግባቡ የመጠቀም፣ የቡና ጥላ ዛፎችን የማልማት እና ያረጁ የቡና ተክሎችን የመጎንደል ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰዋል።
አርሶ አደሩም የድህረ-ምርት አያያዝ ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ እንዲጠቀምና በቡና ልማት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን እንዲያሳድግ በየደረጃው የተቀናጀ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በዘንድሮ የምርት ዘመን 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቶን ቡና በክልሉ ለማምረት ታቅዶ እስከ ግንቦት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ዕቅዱን ሙሉ ለሙሉ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ የታጠበ ቡና እና ደርቆ የተቀሸረ ቡናን ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ሲሰራ የቆየ ሲሆን፣ እስካሁንም ከ350 ሺህ ቶን በላይ ምርት ለማቅረብ ተችሏል።
ከክልሉ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው የቡና ምርት ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ በተሰጠው ትኩረት ከአርሶ አደሩ ማሳ ጀምሮ የቡና ምርት ጥራቱን ጠብቆ እንዲለቀም መደረጉንም ተናግረዋል።
በክልሉ በቡና ልማት ከሚታወቁ አካባቢዎች መካከል የጅማ ዞን አንዱ ሲሆን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሚፍታህ ገቢ በሰጡት አስተያየት፤ በዞኑ በ600 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የቡና ልማት እየተከናወነ ይገኛል።
የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የክልሉ መንግሥት የነደፋቸውን አዳዲስ የቡና ኢኒሼቲቮች በቡና ልማት ለተሰማሩ አካላት የማስተዋወቅ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ በማድረግ እና ዘመናዊ አሰራሮችን በመተግበር ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉን ነው የገለጹት።
በዚህም በዞኑ የቡና ምርታማነትን በአማካይ በሄክታር 11 ኩንታል ማድረስ መቻሉን አቶ ሚፍታህ ተናግረዋል።
በዞኑ በዚህ ዓመት በምርት አሰባሰብ ሒደት የአርሶ አደሩን ግንዛቤ በማሳደግ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ በተሰራው ሥራ እስካሁን ድረስ 41 ሺህ 569 ቶን ቡና መመረቱንም አመልክተዋል።