አገልግሎቱ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን ለማሳለጥ የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አገልግሎቱ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን ለማሳለጥ የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአገሪቱ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን ለማሳለጥ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው ገለጹ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር ያስገነባውን ግዙፍ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ መሙያ ጣቢያ ሥራ አስጀምሯል፡፡
በዚሁ መርሀግብር ላይ የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው በዚሁ ወቀት፤ ተቋሙ እንደ አገር የተያዘውን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ መሠረት በማድረግ አስተማማኝ ኃይል እያቀረበ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ዛሬ ለምረቃ የበቃው ፈጣን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ መሙያ ጣቢያ ለአገልግሎቱ አራተኛው ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም ይህንን መሠረተ-ልማት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች አጠናክሮ ለማስፋፋት መታቀዱን ተናግረዋል።
በተለይም ከፍተኛ ንግድ መስመር በሆነው በኢትዮ-ጅቡቲ ኮሪደር ላይ 16 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ መሙያ ጣቢያዎችን ለመገንባት በአሁኑ ወቅት የዲዛይን ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡