የታዳጊ አትሌቶች ምልመላና ክትትልን ለመደገፍ የሚያስችል አዲስ የዲጂታል ሥርዓት ወደ ስራ ሊገባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የታዳጊ አትሌቶች ምልመላና ክትትልን ለመደገፍ የሚያስችል አዲስ የዲጂታል ሥርዓት ወደ ስራ ሊገባ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2018 (ኢዜአ)፦ በታዳጊ አትሌቶች ምልመላና ክትትል ሂደት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችል አዲስ የዲጂታል ሥርዓት ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችለውን ተግባር እያከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
ከእድሜ ተገቢነት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍም ዲጂታል ቴክኖሎጂው ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም ተመልክቷል።
የጀግኖች አትሌቶች ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ፥ ልጆቿ በየጊዜው የሚያስገኙት ድል ስሟን እያስጠራ፣ ሰንደቅ ዓላማዋም በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ እያደረገ ይገኛል።
ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአትሌቲክሱ ረገድ የሚጠበቀውን ያህል ውጤት እየተመዘገበ አለመሆኑ ይነገራል።
የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ስኬት በከፍታ ለማስቀጠል ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑ እሙን ነው።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አመንሲሳ ከበደ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ የዘርፉን ስኬታማነት ዘላቂ ለማድረግ በታዳጊዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት አማራጭ የሌለው ወሳኝ ተግባር ነው።
በመሆኑም የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ የሀገርን ስም የሚያስጠሩ ውጤታማ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚያስችሉ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ቀርጾ እየተገበረ መሆኑን አመልክተዋል።
ፌዴሬሽኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከታተላቸው ፕሮጀክቶች ወጥ የሆነ የምዘና ሥርዓት እንዲከተሉ በማድረግ፣ የፕሮጀክቶቹ ውጤታማነት ወጣት አትሌቶችን ለማፍራት የሚያስችሉ ሥራዎች መጀመራቸውን አንስተዋል።
አዲሱ አሠራር በፕሮጀክቶች የሚታየውን ደካማ የምዘና ሂደት እና የትጥቅ ድጋፍ በወቅቱ ተደራሽ ያለመሆን ችግሮችን መቅረፉን አስታውቀዋል።
ታዳጊዎችን በፕሮጀክቶች ውስጥ በቅርበት በመከታተል ብቁ አትሌቶችን ለማፍራት የሚያስችል የዲጂታል ሥርዓት ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህ የዲጂታል ሥርዓት በተለይም በእድሜ ዙሪያ ይፈጠር የነበረውን ማነቆ በመቅረፍ፣ አንድ አትሌት በተገቢው የእድሜ ክልል እንዲሳተፍ የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣይ ይህ የዲጂታል ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ ብቁ ወጣት አትሌቶችን ለማፍራት እና የሀገርን ስም እንዲያስጠሩ ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለዋል።