ዩኒቨርሲቲው ለአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ለአካባቢው ስነምህዳር የሚስማሙ ችግኞችን አዘጋጅቷል - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው ለአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ለአካባቢው ስነምህዳር የሚስማሙ ችግኞችን አዘጋጅቷል
አሶሳ፤ ሰኔ 10/2018 (ኢዜአ)፦አሶሳ ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ለአካባቢው ስነምህዳር ተስማሚ የሆኑ ችግኞችን ማዘጋጀቱን አስታወቀ።
በዩኒቨርሲቲው በግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ የደን አያያዝና እንክብካቤ መምህር እና ተመራማሪ አህመድ አሊ እንደገለጹት፣ ዩኒቨርሲቲው ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው።
በየዓመቱ የተለያየ ኢኮኖሚያዊ ጠቃሜታ ያላቸውን የደን እና የፍራፍሬ ችግኞች በማዘጋጀት በራሱ ከሚተክለው ባለፈ ለአካባቢው ማህበረሰብ በማድረስ ለመርሀግብሩ ስኬታማነት የበኩሉን መወጣቱን ገልጸዋል።
ለዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብርም በዩኒቨርሲቲው በሚገኝ የችግኝ ማፍያ ጣቢያ ከ18 በላይ የችግኝ አይነቶችን በማፍላት ለተከላ ዝግጁ ማድረጉን ገልጸዋል።
ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ካላቸውና ከተሻሻሉ ችግኞች መካከል ቡና፣ አቮካዶ፣ ብርቱካን፣ ማንጎ እና ሌሎችም እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
በተለይም ዩኒቨርሲቲው ከጅማ ግብርና ምርምር ያስመጣቸው የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች ለአካባቢው ስነምህዳር ተስማሚ መሆናቸው በመረጋገጡ በቀጣይ ለአካባቢው ማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ ታቅዷል ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የችግኝ ማፍያ ጣቢያ ከ63 ሺህ በላይ ችግኞች መኖራቸውን ገልፀው፣ ችግኝ ጣቢያው በተግባር የታገዘ ትምህርት ለመስጠት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም አስታውቀዋል።
ዩኒቨርሲቲው ባለፈው ዓመት ኡራ እና አቡራሞ ወረዳዎች ላይ የተከላቸው የደን ችግኞች የጽድቀት መጠን በጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑንም አስታውሰዋል።
እንደ መምህርና ተመራማሪ አህመድ ገለጻ በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ሥራዎች የአካባቢን ስነ ምህዳር ከመጠበቅ ባለፈ የደን ሀብት እንዲጨምር አድርገዋል።
ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆን ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆኑንም መምህሩ ጠቁመዋል።