ቀጥታ፡

የሰርኩላር ኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ የኢትዮጵያን ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ የጎላ ሚና አለው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2018 (ኢዜአ)፦ሀገራዊ ሰርኩላር ኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ የኢትዮጵያን ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ የጎላ ሚና እንዳለው በኢትዮጵያ የፊንላንድ ኤምባሲ የትብብር ኃላፊ ቶሚ ሳርኪዮጃ ገለፁ።  

የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር በመተባበር የሀገራዊ ሰርኩላር ኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ ይፋ አድርጓል።

ኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ደረጃ የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ እና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት"የሰርኩላር ኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ" (Circular Economy Roadmap) በማዘጋጀት ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል የማበረታታት ስራዎችን እየሰራች ትገኛለች። 

እንደ አዲስ አበባ ይህንን ፍኖተ ካርታ ወደ መሬት በማውረድ ከከተማዋ እድገት ጋር ተያይዞ የሚመጣውን የቆሻሻ አያያዝ ስጋት ወደ መልካም አጋጣሚ ለመቀየር በርካታ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛሉ።

ይህን በተመለከተ በኢትዮጵያ የፊንላንድ ኤምባሲ የትብብር ኃላፊ ቶሚ ሳርኪዮጃ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ በሰርኩላር ኢኮኖሚ ፖሊሲዎቿና መጠነ-ሰፊ በሆኑ የአካባቢ ጥበቃ መርሃ-ግብሮቿ አማካኝነት ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ አበረታች እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኑን ተናግረዋል።

ፊንላንድ በዚህ ዘርፍ ያላትን ሰፊ ልምድ መሠረት በማድረግ ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ ለኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ዕድሎችን በያዘው የቆሻሻ አወጋገድ እና መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል (ሰርኩላር ኢኮኖሚ) ዘርፍ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እየሠራች መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል።  

ዘርፉ ለአካባቢ ጥበቃም ሆነ ለንግድ ተቋማት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚፈጥር በመሆኑ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰርኩላር ኢኮኖሚ እና መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀትና ዘላቂ የንግድ አሠራሮችን የሚያበረታታ የፖሊሲ ምኅዳር መፍጠሯ አበረታች ነው ብለዋል።

ይህ የሰርኩላር ኢኮኖሚ አጀንዳ ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ-ግብርና ከአረንጓዴ አሻራ ተነሳሽነት ጋር ፍጹም የሚጣጣም መሆኑን ተናግረዋል።

ለአካባቢ ጥበቃና ለዘላቂ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ በመሆናቸው እርስ በርሳቸው የሚደጋገፉ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ረገድ እያገኘች ስላለው ዓለም አቀፍ ዕውቅና ሀገሪቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን (COP32) ለማስተናገድ መመረጧን እንደ ትልቅ ማሳያ ጠቅሰዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም