በዞኑ በአሳታፊ የደን ልማት የአካባቢን ስነ ምህዳር ከመጠበቅ ባሻገር የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በአሳታፊ የደን ልማት የአካባቢን ስነ ምህዳር ከመጠበቅ ባሻገር የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ ተችሏል
ደብረ ማርቆስ ፤ ሰኔ 10/2018 (ኢዜአ)፦ በምስራቅ ጎጃም ዞን በአሳታፊ የደን ልማት የአካባቢን ስነ ምህዳር ከመጠበቅ ባሻገር የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ መቻሉን የዞኑ አካባቢ ጥበቃ ተጠሪ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የተጠሪ ጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ መለሰ መንግስት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ በአሳታፊ የደን ልማት የአካባቢን ስነ ምህዳር ከመጠበቅ ባሻገር የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ ተችሏል።
በዞኑ በመንግስት፣ በግል፣ በማህበራትና በማህበረሰብ ይዞታነት የተመዘገቡ ከ319 ሺህ ሄክታር በላይ ደኖችን በመጠበቅ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታቸውን ለማጉላት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም ደኖችን ከመንከባከብ ባለፈ ነባር ደኖችን ለኢንዱስትሪ ግብዓት በማዋል የተቆረጡትን በአዲስ የመተካት ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ 77 ሺህ 256 ሜትር ኪዩብ የጽድ፣ የባህር ዛፍና ሌሎች የደን ውጤቶችን እንዲሁም 275 ኩንታል እጣን ለሽያጭ በማቅረብ ከ10 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ጠቅሰዋል።
ለኢኮኖሚያዊ ጥቅም የዋለውን ደን ለመተካት ከ570 ሄክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል የጉድጓድ ቁፋሮ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
በደን ልማት ዘርፉም ለ6 ሺህ 343 የህብረተሰብ ክፍሎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል እንደተፈጠረም ተናግረዋል።
በአነደድ ወረዳ የአንበር ዙሪያ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ዋስይሁን ዘሩ፤ በአካባቢያቸው የሚገኘውን የማህበረሰብ ደን በመጠበቅና በመንከባከብ ለምርት ማብቃታቸውን ገልጸዋል።
የደረሰውን ምርት ለእንጨትና ለጣውላ ፋብሪካዎች በመሸጥ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ጠቁመው ለጥቅም የተቆረጠውን ደን መልሰን እየተካን ነው ብለዋል።
የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አቶ እውነቱ ይበልጣል በበኩላቸው፤ የደን ልማት አፈር በጎርፍ እንዳይጠረግ ከማድረጉም በላይ የቀጥታ ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደምም ለምርት የደረሰውን ደን በመሸጥ ለትምህርት ቤት ግንባታ ድጋፍ ማዋላቸውን ጠቁመው አሁን የተገኘውን ገቢም ለማህበራዊ ልማት ለማዋል እየሰራው ነው ብለዋል።