መገናኛ ብዙሃን በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ህዝቡ ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የከፈለውን ዋጋ ለዓለም አሳይተዋል - ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ህዝቡ ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የከፈለውን ዋጋ ለዓለም አሳይተዋል - ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 9/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ህዝብ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ያሳየውን ቁርጠኝነትና የከፈለውን ዋጋ ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ መገናኛ ብዙሃን የጎላ ሚና መጫወታቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ ገለጹ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት "ኢትዮጵያ መርጣለች፣ ኢትዮጵያ አሸንፋለች" በሚል መሪ ሃሳብ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫን የሚመለከቱ መረጃዎችን ከመራጮች ምዝገባ እስከ ምርጫው ዕለት በተከታታይ ለህዝብ በማድረስ ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ልምምድ የላቀ ሙያዊ አስተዋጽኦ ላደረጉ መገናኛ ብዙሃን የምስጋና መርሃ ግብር አካሂዷል።
በሥነ-ስርዓቱ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፣ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ፣ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
ሚኒስትር እናትዓለም በመርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ እውነተኛና ትክክለኛ መረጃን በማስተጋባት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መቆም የመገናኛ ብዙሃን ተቀዳሚ ተግባር ነው።
የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃኑ የሀገርን ዴሞክራሲ በሀገር ልጅ ድምፅ ለዓለም በማስተጋባት ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
ይህም የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም እና ክብር የማስቀደም ጉዳይ በመሆኑ ለቀጣዩ ትውልድ የፀናች ኢትዮጵያን ለማስተላለፍ መሰረት መጣሉን አስገንዝበዋል።
ለአብነትም መገናኛ ብዙሃን ህዝቡ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰለጠነ መንገድ በመምረጥ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሰጠውን ዋጋ በሚገባ ለዓለም ማሳየታቸውን አስረድተዋል።
ከዚህ ባለፈም የፈጠራና የሀሰተኛ መረጃዎችን በማምከን የኢትዮጵያን ስኬት ለማይሹ ሃይሎች ትልቅ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ገልጸው፤ ለዚህም ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋለች ብለዋል።
በቀጣይም ለሀገር አንድነት ይበልጥ በመስራት ለጠንካራ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ገንቢ ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የኢዜአ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ፤ ተቋሙ በዋናነት የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅምና ደህንነት በሚያስከብሩ ትክክለኛ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ እየሰራ መሆኑን አመልክተው፤ ለጠቅላላ ምርጫ ሁሉም ሚዲያዎች በሚባል ደረጃ ፈጣን፣ ትክክለኛ ወቅታዊ መረጃ እንዲያገኙ ማስቻሉን አብራርተዋል።
የኢቢሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቢንያም ኤሮ ፤ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመገናኛ ብዙሃን በጋራና በትብብር በመሥራት የሀገሪቷን ታሪካዊ ጠላቶች ያሳፈሩበት እንደነበር ተናግረዋል።
የኢቢኤስ (EBS) ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ነብዩ ጥዑመልሳን በበኩላቸው፤ በምርጫው ወቅት በመገናኛ ብዙሃን መካከል የታየውን ጠንካራ ቅንጅት አድንቀው፣ ይህም በጋራ ለሀገራዊ ዓላማ የመቆምን አስፈላጊነት ያሳየ ነው ብለዋል።
የኦቢኤን ሥራ አስፈፃሚ ፍስሃ በላይነህ፣ሚዲያው ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ባህል ግንባታን ለማሳደግ በማሰብ የተለያዩ የክርክር መድረኮችን በ19 ቋንቋዎች ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
የአሚኮ ሥራ አስፈፃሚ ሙሉቀን ሰጥዬ፤ መገናኛ ብዙሃን በቅንጅት መስራት ከቻሉ የሀገርን ክብር እና ጥቅም ማስጠበቅ እንደሚችሉ ያረጋገጡበት ነው ብለዋል።
የአሃዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥኝ ስራ አስፈጻሚ ጥበቡ በለጠ፤ ከሂደቱ እንደ ሚዲያ ተቋም ትልቅ ልምድ ማግኘታቸውንና ይህም በቀጣይ ሀገራዊ ጥቅምን የሚያስከብር ተግባራትን በብቃት ለመወጣት እንደሚያስችል ገልጸዋል።