የእንግሊዝ መንግሥት የአቪዬሽን ዘርፉን ለማዘመን ያደረገው የቴክኖሎጂ ድጋፍ የጋራ ደኅንነትን ለማረጋገጥ ያግዛል - ኢዜአ አማርኛ
የእንግሊዝ መንግሥት የአቪዬሽን ዘርፉን ለማዘመን ያደረገው የቴክኖሎጂ ድጋፍ የጋራ ደኅንነትን ለማረጋገጥ ያግዛል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 9/2018(ኢዜአ)፦ የእንግሊዝ መንግሥት የአቪዬሽን ዘርፉን ለማዘመን ያደረገው የቴክኖሎጂ ድጋፍ የጋራ ደኅንነትን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ (ዶ/ር) ገለጹ።
የእንግሊዝ መንግሥት የአቪዬሽን ዘርፉን ለማዘመን ያደረገው 25 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የቴክኖሎጂ እገዛ የርክክብ መርሐ-ግብር እና ጉብኝት በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የአቪዬሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ መከናወኑን አገልግሎቱ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ አመልክቷል።
በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ዳረን ዌልች የተመራ ልዑክ እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት መርሐ-ግብር ላይ የአገልግሎቱ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ድጋፉ በኢትዮጵያና በእንግሊዝ መካከል ያለውን ትብብርና የጋራ ደኅንነትን የማረጋገጥ አጋርነት ማሳያ ነው።
መርሐ-ግብሩ በኢትዮጵያና በእንግሊዝ መካከል ያለውን ዘላቂ አጋርነት የሚያሳይ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ጠቁመው፤ የአቪዬሽን ዘርፉን ለማዘመን የተደረገው የቴክኖሎጂ ድጋፍ በትብብር ስንሰራ በጋራ ደኅንነትና በዓለም አቀፍ ትስስር አውድ የምናሳካቸውን ድሎች ያሳያል ብለዋል።
የአቪዬሽን ደኅንነት ስጋት ተለዋዋጭና በየጊዜው እያደገ የሚመጣ የዘርፉ ፈተና ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ያለውን የበላይነት አስጠብቆ ለመዝለቅ የደኅንነት ስጋቶችን አስቀድሞ በማወቅ ማስቀረት ወሳኝ ተልዕኳች ነው ያሉት ዶ/ር ሲሳይ፤ የቴክኖሎጂ ድጋፉ የመፈጸም አቅምን ያሳድጋል ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያና እንግሊዝ ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመው፤ በተለይ በቢሾፍቱ የሚገነባው አዲሱ የአየር ማረፊያና ሀገሪቱ እ.አ.አ በ2027 የምታስተናግደው የኮፕ-32 ጉባኤ በተለያዩ የአጋርነት ማዕቀፎች የሚገለጹ ወሳኝ ሁነቶች መሆናቸውን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በዓመት እስከ 120 ሚልየን መንገደኞችን የሚያስተናግድ በአፍሪካ ግዙፍ የሆነ አየር ማረፊያ እየገነባች መሆኑን አመልክተው፤ ይህ ከአቪዬሽን ደኅንነት አኳያ ከፍተኛ ዝግጁነት እንደሚፈልግ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ዳረን ዌልች በበኩላቸው፤ ሁለቱ ሀገራት እስከ ዛሬ የዘለቀና ጠንካራ ወዳጅነት እንዳላቸው ጠቁመዋል።
የአቪዬሽን ዘርፉን ለማዘመን የተደረገው እገዛ ይህንኑ የሚመሰክርና የሚያጠናክር መሆኑንም አመልክተው ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፍ ያላት ቁመና የሚደነቅ መሆኑንም መስክረዋል።
በየእለቱ የምታከናውኑት ተግባር የሀገሪቱንም የእኛንም ደኅንነት ስለሚያረጋግጥ አድናቆቴን መግለጽ እወዳለሁ ያሉት አምባሳደሩ የቦሌ ዓለም-አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቁልፍ የሆነ የዓለም-አቀፍ ተጓዞች መዳረሻና ማዕከል ነው፡፡ ደኅንነትን የማረጋገጥ ጉዳይ የሁላችንም የጋራ ኃላፊነት መሆኑ ይታወቃል ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከሰቱ ያሉ የበረራ ደኅንነት ስጋቶችን ለመቀነስ ዘመናዊ መሣሪያዎችን መታጠቅ መፍትሔ ስለሚሆን በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ስራ ላይ የሚውል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለኢትዮጵያ መበርከቱንም ተናግረዋል።
የአቪዬሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ ዳይሬክተር አስራት ቀጄላ፤ ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፍ ዓለም-አቀፍ መመዘኛዎችን በብቃት በማሟላት ተጠቃሽ ሀገር መሆኗን አረጋግጠዋል።
የእንግሊዝ መንግሥት ድጋፍም በተለያየ መንገድ ሲገለጽ መቆየቱን አመልክተው፤ ለተደረገው እገዛም ምስጋና አቅርበዋል። ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር በተለያዩ የተቋማዊ ግንባታ መስኮች ዘርፈ ብዙ ትብብሮችን ስናደርግ ቆይተናል ይህም ለኢቪዬሽንና ለዓለም-አቀፍ አየር ትራንስፖርት ዘርፍ ደኅንነት መረጋገጥ ጉልህ ሚና ወደ ሚያበረክት ስትራቴጂክ ምዕራፍ ተሸጋግሯል ሲሉም ገልጸዋል።
የአቪዬሽን ዘርፉን ለማዘመን የተደረገው ድጋፍ ዘመኑን የዋጀ የበረራ ደኅንነትን ለማከናወን ከፍተኛ ሚና እንደሚያበረክት አቶ አስራት አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምባሲ በኩል የተደረገው ድጋፍ ከሀገሪቱ ‹‹ሆም ኦፊስ ኢንተርናሽናል ኦፕሬሽን›› ቢሮ የተገኘ መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን የላከው መረጃ ጠቁሟል።