ቀጥታ፡

የቱሪዝም ዘርፉን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማዘመን እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 9/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አማራጮችን በመጠቀም የቱሪዝም ዘርፉን ለማዘመን እየሰራች መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትር ዴኤታው ከዓለም አቀፉ የብራንዲንግ እና ሚዲያ ተቋም "FAME by Sheeraz" መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ሺራዝ ሀሰን እና የልዑካን ቡድናቸው ጋር በቱሪዝም ዘርፍ በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

እንደገና አበበ (ዶ/ር) መንግስት ባለፉት ስምንት ዓመታት አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በመገንባት፣ ነባሮቹን በማደስ እና የዲጂታል ቴክኖሎጂን (Visit Ethiopia Portal) በመጠቀም ዘርፉን ለማዘመን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም አዲስ አበባን የአህጉሪቱ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየተደረገ ያለውን ጥረት ጠቅሰው፤ እንደ "FAME by Sheeraz" ባሉ ተቋማት አማካኝነት የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተዋወቅ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የ"FAME by Sheeraz" መስራች ሺራዝ ሀሰን በበኩላቸው፣ ድርጅታቸው በአሜሪካ፣ በአውሮፓ እና በመካከለኛው ምስራቅ ታዋቂ ግለሰቦችን እና የንግድ ምልክቶችን በማስተሳሰር የረጅም ጊዜ ልምድ እንዳለው ገልጸዋል።

ይህንን ልምድ በመጠቀም የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት በጋራ ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው የገለጹት ዋና ስራ አስኪያጁ፤ ለተግባራዊነቱም ተቋሙ በአዲስ አበባ ቋሚ ጽሕፈት ቤት እንደሚከፍት ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የታገዙ የመገናኛ ብዙኃን አማራጮችን በመጠቀም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ስትራቴጂያዊ እቅድ ቀርጸው ለመንቀሳቀስ ዝግጁ መሆናቸውን ነው ዋና ስራ አስኪያጁ ያረጋገጡት።

በውይይቱ ወቅት፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል የተነሱትን ነጥቦች ወደ ተግባር ለመቀየር ስምምነት ላይ መደረሱን የቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም