ቀጥታ፡

የከተማዋ እድገት ተደማሪና ቀጣይነት ያለው እንዲሆን አመራሩ በቁርጠኝነትና በተደራጀ መንገድ ሊመራ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 9/2018 (ኢዜአ)፡-የአዲስ አበባ ከተማ እድገት ሁልጊዜም ተደማሪና ቀጣይነት ያለው እንዲሆን አመራሩ በቁርጠኝነትና በተደራጀ መንገድ ሊመራ እንደሚገባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የከተማ አስተዳደሩ በቀጣዮቹ 90 ቀናት መሪ ዕቅድ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ አካሂዷል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ባለፉት ጊዜያት የተመዘገቡ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና በከተማዋ የተጀመሩ ግዙፍ የልማትና የሪፎርም ሥራዎችን በላቀ ፍጥነት ለማጠናቀቅ የ90 ቀናት መሪ ዕቅዱ ሚና የጎላ ነው ብለዋል። 

ዕቅዱ በዋናነት የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት፣ አገልግሎት የማሻሻል ስራን በማጠናከር የመሶብ አንድ ማእከል ዲጂታል አገልግሎትን ማስፋት፣ የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት፣ የንግድ ስርዓቱን መግራት፣ የስራ እድል ፈጠራ እና የወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚነት ላይ መስራት ነው ብለዋል።

እንዲሁም የአረንጓዴ አሻራ ልማት፣ የከተማ ግብርና እና የሌማት ትሩፋት፣ የሰላም ግንባታ ስራዎች፣ የገቢ አሰባሰብ፣ ልመናንና ተረጂነትን መቀነስ፣ የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብርን በተቀናጀ የህብረተሰብ ተሳትፎ መተግበር፣ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን በአዲስ ቅኝት መምራት እና ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ የእቅዱ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የተጀመሩ የኮሪደር ልማት እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎችን በጥራት እና በተያዘላቸው የጊዜና በጀት ማጠናቀቅ እና የሚዲያና የህዝብ ግንኙነት ስራዎችን ለማጠናከር መታቀዱን ተናግረዋል።

የታቀዱ ግቦችን ለማሳካት በየደረጃው የሚገኘው አመራር በቁርጠኝነትና በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት መሥራት እንደሚኖርበትም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በመድረኩ ላይ የቀረቡት የመንግሥትና የፓርቲ ዕቅዶች ከተማዋን ምቹ፣ ፅዱና ዘመናዊ የማድረግ ራዕይን መሠረት ማድረጋቸውንም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።

የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብና ጥራት እንዲጠናቀቁ የሚያስችሉ በመሆናቸው ለዕቅዶቹ መሳካት መትጋት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው፤ በመጪዎቹ ሦስት ወራት አመራሩ በተሟላ አግባብ ለሕዝብ ቁርጠኛ አገልግሎት የሚሰጥበት ጊዜ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል። 


 

ከተማዋ በአሁኑ ወቅት እጅግ በርካታና ዕረፍት የሚነሱ ሥራዎች ያሉባት መሆኑን ገልጸው፤ ይህንንም አመራሩ ሊገነዘብ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በክረምቱ ወቅት የሚከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ ከወትሮው አገልግሎት ውጭ ያሉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እና የፕሮጀክት ክዋኔዎች ከፍተኛ ትኩረት የሚሹ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

ለዚህም አመራሩ ፕሮጀክቶችን ከተቀመጠላቸው ጊዜ ቀድሞ ለማጠናቀቅ የሚያስችል ከፍተኛ ተነሳሽነትን ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።


 

በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ፤ በቀጣዮቹ ቀናት በአመራሩና በመዋቅሩ ውስጥ አዲስ የሥራ ተነሳሽነትና ጥንካሬ መፈጠር እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል። 

አሁን መዋቅሩንና አመራሩን በከፍተኛ ደረጃ በማነቃቃት እንዲሁም አባላትን በማስተባበር በ90 ቀናቶቹ የታቀዱት ሥራዎች ላይ የተጠናከረ የሥራ አፈጻጸም ማምጣት እንደሚገባና ለዚህም ዝግጁነትን አጠናክሮ መሄድ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም