የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን በህዝቦች አብሮነትና ትውልድ ቀረጻ ላይ ድርብ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን በህዝቦች አብሮነትና ትውልድ ቀረጻ ላይ ድርብ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 9/2018(ኢዜአ)፦ የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን በህዝቦች አብሮነትና ትውልድ ቀረጻ ላይ ድርብ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ ገለጹ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን እና የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ ይዘቶችን በጋራ መቆጣጠር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ በሃይማኖት ሽፋን የሚሰራጩ ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን፣ የጥላቻ ንግግሮችንና ሐሰተኛ መረጃዎችን በጋራ በመከላከል በኩል ጥብቅ ሥርዓት ለመዘርጋት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
በሥነ ሥርዓቱም የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተፈጠረው ምቹ ምህዳር እስካሁን 51 የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል።
ተቋማቱ በአብሮነትና ኢትዮጵያዊ እሴት ግንባታ በትብብር እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው፤ የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃንም በህዝቦች አብሮነትና ትውልድ ቀረጻ ድርብ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።
በአንጻሩ በዲጂታል አውታሮች ግጭት የሚቀሰቅሱና የሃይማኖት እሴቶችን የሚሸረሽሩ አንዳንድ መረጃ አሰራጮችን የአሰራር ጥሰቶች ማጋለጥና መታገል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የትብብር ስምምነት ፊርማውም የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ሥርጭትን በተቀናጀ አግባብ ለመከላከል አስቻይ ሁኔታ እንደሚፈጥር አብራርተዋል።
ስምምነቱ የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያዊ እሴቶችን የሚያጎለብቱ ተግባራትን ማከናወናቸውን ማረጋገጥ የሚያስችል ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሃይማኖቶች መካከል ተቃርኖና ግጭች ቀስቃሽ መልዕክቶችን የሚያሰራጩ አካላትን ለመከላከል የ9192 ነጻ ስልክ መስመርና "ኤማ" የተሰኘ መተግበሪያ (EMA APP) ሥራ ላይ ማዋሉን አክለዋል።
ሕግ አክብረው በማይሰሩ የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ላይ ተጠያቂነትን ለማስፈን ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሃፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው፤ ሥምምነቱ የኃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ሀገር ወዳድ ዜጋ በማፍራት መንፈሳዊ ግዴታቸውን በተሻለ መልኩ እንዲወጡ ያግዛል ብለዋል።
የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ከልዩነት ይልቅ አንድ የሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ በመሥራት ለዘላቂ ሰላምና የህዝብ አብሮነት በላቀ ደረጃ ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በቀጣይም የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት እንደሚጠናከር ተናግረዋል።