ቀጥታ፡

ቡናን በበጋ መስኖ በማልማት የአምራቹን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል

አዳማ፤ ሰኔ 9/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ቡናን ከመደበኛ ወቅት በተጨማሪ በበጋ መስኖ በማልማት የአምራቹን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት መደረጉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው የክልሉን የቡና ምርትና ምርታማነትን በበጋ መስኖ ለማስፋፋት ያዘጋጀው የባለሙያዎችና አመራሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ይገኛል።


 

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሀመድ ሳኒ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ አዲስ የቡና፣ ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ኢኒሼቲቭ ፓኬጅ ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ ልማቱን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ፣ ከአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ጋር እያጋጠመ ያለውን የቡና ተባይና በሽታን ለመቋቋም የሚያስችል ስትራቴጂ ተነድፎ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተያዘው ስትራቴጂ ላይ ግንዛቤ እንዲፈጠር ለባለሙያዎችና ለአመራሮች ስልጠናው መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

በዚህ ረገድ በክልሉ በጥቂት ባለሀብቶች የተጀመረውንና ውጤት የተገኘበትን የበጋ መስኖ ቡና ልማት ተሞክሮ በመቀመር ወደ አርሶ አደሩ ለማስፋፋት አቅጣጫ መያዙን አስታውቀዋል።

ለዚህም በየደረጃው ለሚገኙ አርሶ አደሮች የክህሎት ስልጠና በመስጠት እና የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ማዳበሪያን በማመጣጠን የቡና መስኖ ልማትን ለማስፋፋት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በዚህም አሁን ላይ በክልሉ ከአንድ ሄክታር ላይ የሚገኘውን ዘጠኝ ኩንታል ምርት ወደ 20 ኩንታል ለማሳደግ ግብ መያዙን አብራርተዋል።

በቀጣይም እስከ ቀበሌ ድረስ ስልጠናዎችን በመስጠት እና የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን በመትከል እንዲሁም የቡና ልማትን በኩታገጠም እንዲታረስ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ተፈጻሚ እንደሚደረግ አስረድተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ተሾመ ቦጋለ በበኩላቸው፤ ቡናን በመስኖ በማልማት በሄክታር ከ30 እስከ 40 ኩንታል ምርት ማግኘት እንደሚቻል ገልጸዋል።

ይህ ብቻ ሳይሆን በቂ ሙያዊ ድጋፍ ከተደረገ በዓመት ሁለት ጊዜ ምርት እንደሚሰጥም ተረጋግጧል ብለዋል።


 

በመሆኑም አርሶ አደሩ ያረጁ የቡና ዝርያዎችን በተሻሻሉ ዝርያዎች በመተካት እና በቂ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ማዳበሪያን በማመጣጠን ምርታማነቱን እንዲያሳድግ ኢንስቲትዩቱ ቴክኖሎጂ የማስተዋወቅ ስራ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

እውቀት፣ ክህሎት፣ ቴክኖሎጂ እና የተፈጥሮ ጸጋን በማቀናጀት በጥቂት ዓመታት ውስጥ የቡና ምርታማነትን ከእጥፍ በላይ በማሳደግ ዘርፉ ለውጭ ምንዛሪ ግኝቱ የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚቻልም አረጋግጠዋል።

ለአራት ቀናት በተዘጋጀው የአሰልጣኞች ስልጠና መድረክ ላይ ከክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የተውጣጡ ከ1 ሺህ 500 የሚበልጡ የግብርና ባለሙያዎችና አመራሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም