የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ምክክሩ መምጣታቸው ለዘላቂ ሰላም ጉልህ ሚና አለው - የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ምክክሩ መምጣታቸው ለዘላቂ ሰላም ጉልህ ሚና አለው - የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 9/2018(ኢዜአ)፦ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ምክክሩ መምጣታቸው ለዘላቂ ሰላም ጉልህ ሚና የሚጫወትና ሌሎችም ተመሳሳይ መንገድ እንዲከተሉ በር የሚከፍት መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ።
አሁንም በሰላማዊ መንገድ አጀንዳዎቻቸውን ለሚያቀርቡ ታጣቂዎች በሩ ክፍት መሆኑን ተናግሯል።
በኦሮሚያ ክልል ወደ ሰላም የተመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎች አጀንዳዎቻቸውን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረክበዋል።
በኦሮሚያ ክልል ወደ ሰላም የተመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎች የአጀንዳ ማሰባሰብና የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የተሳታፊዎች ልየታ ለሁለት ቀናት በአዳማ ተካሂዷል።
የቀድሞ ታጣቂዎቹን አጀንዳዎች የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረስላሴ ተረክበዋል።
ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ በዚሁ ወቅት፣ ዕለቱ ለኮሚሽኑም ሆነ ለሀገሪቱ የሰላም ጉዞ ትልቅ ምዕራፍ የተከፈተበት ነው ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በትጥቅ ትግል ላይ የቆዩ በርካታ ወጣቶች ወደ ሰላም በመምጣት፣ በኮሚሽኑ መድረክ ላይ በመገኘት ፍላጎቶቻቸውን በግልጽ የሚያሳዩ አጀንዳዎችን በይፋ አስረክበዋል ነው ያሉት።
ይህ መድረክ ወጣቶቹ ያለምንም ተፅዕኖ ሀሳቦቻቸውን በነጻነት የገለጹበት መሆኑንም አክለዋል።
ይህን መሰል አርዓያነት ያለው ሂደት ከዚህ ቀደም በአማራ ክልልም በተመሳሳይ መካሄዱን አስታውሰዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎች ሰላም የተሻለ አማራጭ መሆኑን አምነው በመድረኩ መሳተፋቸው ችግሮችን በምክክር የመፍታት እርምጃን የሚያጎለብት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በአጀንዳዎች ላይ ምክክር ተደርጎ የጋራ መፍትሔ እንዲመጣ ኮሚሽኑ የተለመደ ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ዋናውን ሀገራዊ ምክክር ለመጀመር የቀረው አንድ ወር ገደማ መሆኑን ጠቁመው፣ ኮሚሽኑ በሰላማዊ መንገድ አጀንዳዎቻቸውን ለሚያቀርቡ ታጣቂዎች በሩ ክፍት መሆኑን አስታውቀዋል።
በመሆኑም በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ አካላት ወደ ሀገራዊ ምክክሩ እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።