በቀጣዮቹ 90 ቀናት የመዲናዋን ነዋሪዎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሠራል - ኢዜአ አማርኛ
በቀጣዮቹ 90 ቀናት የመዲናዋን ነዋሪዎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሠራል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 9/2018 (ኢዜአ)፡-የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቀጣዮቹ 90 ቀናት የከተማዋን ነዋሪዎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ላይ በትኩረት እንደሚሠራ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የከተማ አስተዳደሩ በቀጣዮቹ 90 ቀናት መሪ ዕቅድ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ባለፉት ጊዜያት የተመዘገቡ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና በከተማዋ የተጀመሩ ግዙፍ የልማትና የሪፎርም ሥራዎችን በላቀ ፍጥነት ለማጠናቀቅ የ90 ቀናት መሪ ዕቅዱ ሚና የጎላ ነው ብለዋል።
ዕቅዱ በዋናነት የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የኮሪደር ልማት፣ የገቢ መሰብሰብ፣ የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የኑሮ ውድነት ማቃለል፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የክረምት በጎፈቃድ እና በመሶብ አንድ ማዕከል የሚሰጡ አገልግሎቶች ማብዛት እና ሌሎች ስትራቴጂካዊ ተግባራት ላይ ትኩረት ማድረጉን ጠቁመዋል።
እንዲሁም የከተማ ግብርና፣ የሌማት ትሩፋት፣ የትምህርት ዘርፍ ማጠቃለያ እና የዝግጅት ምዕራፍ፣ የጎርፍ መከላከል ሥራ በትኩረት እንደሚከናወኑም አንስተዋል።
የታቀዱ ግቦችን ለማሳካት በየደረጃው የሚገኘው አመራር በቁርጠኝነትና በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት መሥራት እንደሚኖርበትም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በመድረኩ ላይ የቀረቡት የመንግሥትና የፓርቲ ዕቅዶች ከተማዋን ምቹ፣ ፅዱና ዘመናዊ የማድረግ ራዕይን መሠረት ማድረጋቸውንም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብና ጥራት እንዲጠናቀቁ የሚያስችሉ በመሆናቸው ለዕቅዶቹ መሳካት መትጋት እንደሚገባ ተናግረዋል።