የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ሰላምና ልማት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የተቀናጀ ስራን ማጠናከር ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ሰላምና ልማት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የተቀናጀ ስራን ማጠናከር ወሳኝ ነው
ጅግጅጋ፤ ሰኔ 9/2018 (ኢዜአ)፡-የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ሰላምና ልማት በዘላቂነት ለማረጋገጥ፣ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ የተቀናጀ ስራን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ዑስማን ገለጹ።
ሀገር አቀፍ የአርብቶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደር ክልሎች የሰላም ፎረም ምስረታ መድረክ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
ይህ ፎረም በአርብቶ አደሩ አካባቢዎች ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማጠናከር የተጀመሩ ጥረቶችን ይበልጥ ለማጎልበት ያለመ እንደሆነም ታውቋል።
የመድረኩ ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ የአርብቶ አደር አካባቢዎች በሚገኙ የሰላም እና ጸጥታ ቢሮዎች እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል የጋራ የትብብርና የአጋርነት ፎረም ማቋቋም መሆኑም እንዲሁ።
የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ዑስማን በወቅቱ እንዳሉት፤ ይህ መድረክ የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ የኑሮ ዘይቤ ለመቀየርና በአካባቢው አስተማማኝ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የጎላ ሚና ይኖረዋል።
አርብቶ አደሮች ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ በመሆኑ በክልሎች መካከል ትብብርን ለማጠናከርና የልምድ ልውውጥና የህዝብ ለህዝብ መደጋገፍን ለማሳደግ የሚረዳ ነው ብለዋል።
ፎረሙ የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ሰላምና ልማት በተመለከተ የሚነሱ ችግሮችን በሳይንሳዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል በመሆኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።
በመድረኩ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ቸሩጌታ ገነነ፤ በሀገሪቱ የአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ሰፊ ህዝብና መሬት፣ ግዙፍ የእንስሳት ሀብት፣ እምቅ የከርሰ ምድር ማዕድናት እንዲሁም ለታዳሽ ኃይል ልማት እጅግ ተስማሚ የሆኑ እምቅ አቅሞች ያሉባቸው ናቸው ብለዋል።
እነዚህ አካባቢዎች ለዘመናት የቆዩ ማህበራዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ ጠንካራና የዳበሩ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስልቶችና እሴቶች ባለቤት መሆናቸውንም አክለዋል።
ባህላዊ እሴቶቹም ለሀገራዊ ሰላምና አንድነት መሠረት ቢሆኑም፣ ውስጣዊ ውስንነቶች ማህበረሰቡ ከልማቱ ሙሉ በሙሉ እንዳይጠቀም ማነቆ ሆነው መቆየታቸውን ሚኒስትር ዴኤታው አስገንዝበዋል።
እነዚህን ተግዳሮቶች በዘላቂነት ለመፍታት ጠንካራ ቅንጅታዊ አሠራርን መዘርጋት የግድ እንደሚል አንስተው፤ በተለይም የማህበረሰቡን የኑሮ ዘይቤ ለመቀየር የጋራ ቅንጅትን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በሀገሪቱ የሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን ሳይንሳዊና ዘላቂ በሆነ መንገድ ለመፍታት ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚጫወቱት ሚና እጅግ ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በመድረኩ የኦሮሚያ፣ የሶማሌ፣ የአፋር፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች ተወካዮች እየተሳተፉ ሲሆን የፌዴራልና የክልሎቹ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ሃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶችም ታድመዋል።