በክልሉ የሌማት ትሩፋት ትግበራ የወተት ምርታማነት እንዲጨምር አስተዋጽኦ አበርክቷል - ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የሌማት ትሩፋት ትግበራ የወተት ምርታማነት እንዲጨምር አስተዋጽኦ አበርክቷል - ቢሮው
ሆሳዕና፤ ሰኔ 9/2018 (ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሌማት ትሩፋት የወተት ልማት ምርታማነት እንዲጨምር አስተዋጽኦ ማበርከቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ።
የሌማት ትሩፋት መርሀግብር የምግብ ሉአላዊነትን የማረጋገጥና ክብርን የማስጠበቅ ዓላማ ያለው ሲሆን በተለይ በወተት፣ ሥጋ፣ እንቁላልና ማር ትርፍ ምርት በማምረት መጠቀም ላይ ያተኮረ ነው።
መርሀግብሩ የኢትዮጵያን ደካማ አምራችነት ታሪክ በመቀየር የምግብ ሉአላዊነትን ማረጋገጥና የኢኮኖሚ እድገትን የማፋጠን ግብም አለው።
መርሃ ግብሩ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ በኋላም የወተት ምርታማነትን በማሳደግ ዜጎችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እያደረገና ገበያን ለማረጋጋት አቅም እየፈጠረ መጥቷል፡፡
በጉዳዩ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር እንደገለፁት፣ በክልሉ የሌማት ትሩፋት መርሀግብር የወተት ምርታማነት ለማሳደግ፣ የእንስሳት ዝርያን ለማሻሻል፣ የመኖ አቅርቦት እንዲጠናከር እንዲሁም በእንሰሳት ጤና አጠባበቅ ላይ ውጤት አምጥቷል።
የወተት ምርታማነት ከማሳደግ ባለፈ የገበያ ትስስርና እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ ላይ በመሰራቱ በክልሉ 12 የወተት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች እንዲቋቋሙ መደላድል መፈጠሩንም አቶ ኡስማን ጠቅሰዋል።
በሆሳዕና ከተማ በእንስሳት እርባታ ዘርፍ የተሰማሩት አቶ አዳነ አባቴ እንደገለፁት ወደዘርፉ ከገቡ ሰባት ዓመታትን ቢያስቆጥሩም በተሻለ ተጠቃሚ ሳይሆኑ ቆይተዋል።
የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ትግበራን ተከትሎ መንግስት በዘርፉ የተሰማሩ ዜጎች እንዲጠቀሙ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ሥራ መስራቱ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።
በዚህም ዝርያቸው የተሻሻሉ ጥጆችን በማግኘት የወተት ምርታማነትን እያሳደጉ ከመምጣታቸው ባለፈ ገቢያቸውም እንዲጨምር ማድረጉን ገልጸዋል።
በሀድያ ዞን ሌሞ ወረዳ ሹርሞ ዊጥቢራ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ዘነበች ጋርከቦ በበኩላቸው እንዳሉት በሌማት ትሩፋት መረሀ ግብር ታቅፈው የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው ላሞችን በማርባት በወተት ልማት ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።
መንግስት በፈጠረው ዕድል ተጠቅመው ከዚህ ቀደም የነበሯቸውን የወተት ላሞች ዝርያ በተሻሻሉ ዝርያዎች በመተካት ምርታማነታቸውን እያሳደጉ መሆኑን ገልጸዋል።