የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን በሀሰተኛ መረጃ እና ጥላቻ ንግግር መከላከል ላይ ሚናቸውን የበለጠ ሊያጠናክሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን በሀሰተኛ መረጃ እና ጥላቻ ንግግር መከላከል ላይ ሚናቸውን የበለጠ ሊያጠናክሩ ይገባል
አዲስ አበባ፤ሰኔ 9/2018 (ኢዜአ)፡-የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን በሀሰተኛ መረጃ እና ጥላቻ ንግግር መከላከል ላይ ሚናቸውን የበለጠ ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ገለጸ።
ባለስልጣኑ ሀሰተኛ መረጃ ስርጭትና ጥላቻ ንግግርን በጋራ ለመከላከል የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ከኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ እና የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸኃፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ተፈራርመውታል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ በዚሁ ወቅት፤ ለውጡን ተከትሎ በተፈጠረው ምቹ ምህዳር እስካሁን 51 የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸዋል።
ተቋማቱ በአብሮነት፣በመከባበርና በኢትዮጵያዊ እሴት ግንባታ ላይ በትኩረት እየሰሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
በአንጻሩ በዲጂታል አውታሮች ግጭት የሚቀሰቅሱና የሃይማኖት እሴቶችን የሚሸረሽሩ አካላትን ለመከላከል ስምምነቱ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
ለዚህም ባለስልጣኑ በዲጂታል አውታሮች የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮችን ሪፖርት ማድረግ የሚያስችል "ኤማ" የተሰኘ መተግበሪያ (EMA APP) እና የ9192 ነፃ የስልክ መስመር ስራ ላይ ማዋሉን አስታውቀዋል።
ባለስልጣኑ ህግ አክብረው በማይሰሩ መገናኛ ብዙሃን ላይ ተጠያቂነትን ለማስፈን ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በትብብር እንደሚሰራ የገለጹ ሲሆን፣ ለዚህም አስፈላጊውን የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸኃፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን በፈቃዳቸው መሰረት እንዲሰሩ ማስቻልና የአቅም ግንባታ ትብብርን ማጠናከር ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል።
ሃይማኖትን ማስኬድ የሚቻለው ሰላም ሲኖር ብቻ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ጸኃፊው፣ የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ለዘላቂ ሰላምና ለህዝቦች አብሮነት በላቀ ደረጃ ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።