የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት የጽሑፍ ሀብቶችን ወደ ዲጂታል የመቀየር ሥራ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት የጽሑፍ ሀብቶችን ወደ ዲጂታል የመቀየር ሥራ ጀመረ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 9/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ዘመናዊ የቤተ መጻሕፍት ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችለውን የጽሑፍ ሀብቶችን ወደ ዲጂታል የመቀየር ሥራ በይፋ ጀምሯል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ 20 ሚሊዮን ገጾችን ወደ ዲጂታል የመቀየር ስራ እንደሚከናወን ተገልጿል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፣የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰርፀ ፍሬስብሐት እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፤ ዘመናዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር እና የተሟላ ዲጂታል ኢኮኖሚ እውን ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአብነትም ከወረቀት አሠራር ወደ ዲጂታል የመሸጋገር እና የታሪክ ሀብቶችን ወደ ዲጂታል ቋት በማስገባት ለቀጣይ ትውልድ የማስተላለፍ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት የጀመረው ጉዞም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ አካል ሲሆን፣ በቀጣይ በሁሉም ዘርፎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያነሱት።
በቤተ መጻሕፍቱ የሚገኙ የሀገር ሀብቶችን ጠብቆና ተንክባክቦ ለቀጣይ ትውልድ ለማሻገር የዲጂታላይዜሽን ሥራው ወሳኝ መሆኑን ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት የሀገር ታሪክ፣ ባህል እና ማንነት የተሰነደበት ማዕከል መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ የተጀመረው የዲጂታላይዜሽን ሥራ ታሪካችንን ለቀጣይ ትውልድ በታማኝነት ለማስተላለፍ እና ማንኛውም ሰው የሚፈልገውን መረጃ በቀላሉ እንዲያገኝ ያስችላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰርፀ ፍሬስብሐት አገልግሎቱ ባለፉት 83 ዓመታት በርካታ ታሪካዊ መረጃዎችን በመሰነድ እና በማስቀመጥ ለትውልድ ሲያስተላልፍ መቆየቱን አስታውሰዋል።
አሁን እየተሠራ ያለው የጽሑፍ ሀብቶችን ወደ ዲጂታል የመቀየር ሥራ የሀገሪቱን የመረጃ ሀብቶች በማሰባሰብ እና በማደራጀት ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ያስችላል ብለዋል።
ይህም ማንኛውም ሰው መረጃዎችን በዲጂታል መንገድ በቀላሉ እንዲያገኝ ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት።
በወረቀት ላይ የሰፈሩ ታሪካዊ መረጃዎች ከጊዜ ብዛትና ከአያያዝ ጉድለት እንዳይጠፉና እንዳይበላሹ ዘላቂ ጥበቃ ለማድረግ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።