ብርሃንን እና እስትንፋስን የመለሰ የደግነት ተግባር - ኢዜአ አማርኛ
ብርሃንን እና እስትንፋስን የመለሰ የደግነት ተግባር
የዓይን ብርሃንን በለጋነት ዕድሜ ማጣት ፈታኝ ክስተት ነው። እንደ ዕድሜ እኩዮች በነፃነት የመቦረቅ ፍላጎትን የሚገታ፣ ማህበራዊና ስነልቦናዊ ጫናዎችንም የሚፈጥር አጋጣሚ ነው። ይህ ፈተና በአንዳንዶች ላይ ፍፁም ተስፋ መቁረጥንም ሊፈጥር እንደሚችል የዛሬ ባለታሪካችን ምስክር ነው።
ወጣት ታሪኩ ሁሴን በለጋ ዕድሜው በአንድ ዓይኑ ላይ ባጋጠመው የዓይን ብሌን ጠባሳ ሳቢያ ነበር እይታውን ያጣው።
በልጅነት ዕድሜው የገጠመው ይህ ድንገተኛ መሰናክል፣ እንደ እኩዮቹ በነፃነት ለመጫወትና በትምህርት ገበታው ላይ በለመደው መንገድ ለመጓዝ ትልቅ ፈተና ሆኖበት ቆይቷል።
ዕድሜው እየጨመረ ሲሄድ፣ ችግሩ በእሱ ላይ ብቻ የመጣ መስሎት ፈጣሪን ይወቅስ፤ ያማርር እንደነበርም ይናገራል፤ ለከፋ የስነልቦና ቀውስም መዳረጉን ያነሳል ወጣት ታሪኩ።
ይባስ ብሎም፣ ላጋጠመው ህመም ብቸኛው መፍትሔ የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ መሆኑንና ያኔ ህክምናው በሀገር ውስጥ እንደማይገኝ ሲሰማ ስጋቱና ትካዜው እጥፍ ድርብ ሆነ፤ ተስፋ ለመቁረጥም ተዳረገ።
ነገር ግን የሰው ልጅ የማይነጥፍ ደግነትና የተቋማት ጥረት የታሪኩን ህይወት ቀየሩት። ዕድሜ ለዓይን ባንክ ይሁንና፣ ታሪኩ ከ13 ዓመታት በፊት በዳግማዊ ምኒልክ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ህክምና አገኘ።
ዛሬ ላይ ያንን አስቸጋሪ ጊዜ አልፎ፣ የልጅነት ህልሙን አሳክቶ በትምህርቱና በህይወቱ ስኬታማ መሆኑን በደስታና በፈገግታ ይናገራል።
በደጋግ ኢትዮጵያውያን በጎ ፈቃደኝነት በተበረከተልኝ የዓይን ብሌን ስጦታ ብርሃኔን መልሼ አግኝቻለሁ። ይህ ስጦታ በገንዘብ የማይገዛ ውድ ስጦታ ነው ይላል ወጣት ታሪኩ።
ታሪኩ የችግሩን ስፋትና የእይታ እክል የሚያመጣውን ማህበራዊ ጫና በተግባር በመረዳቱ፣ ዛሬ እሱ ራሱ ለሌሎች ተስፋ ለመሆን ተነሥቷል። ሌሎች ደጋግ ዜጎችም የዓይን ብሌናቸውን በመለገስ ለወገኖቻቸው ብርሃን እንዲሆኑ የበኩሉን ጥረት እያደረገ ይገኛል።
ለዚህም ይረዳ ዘንድ "የኢትዮጵያ ብሔራዊ የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ የተደረገላቸው በጎ ፈቃደኞች ማህበር መስረተናል ነው ያለው።
ማህበሩ የዓይን ብሌን የተለገሱ ሰዎችን ህያው ምስክርነት በመጠቀም፣ ማህበረሰቡ ለልገሳ ያለውን ግንዛቤ እንዲያሳድግ ከኢትዮጵያ ደም እና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል።
የዓይን ብሌን ልገሳ ከዚህ ዓለም ስንሰናበት ለሌላ ሰው የዕይታ ምንጭ ሆነን የምናልፍበት ታላቅ ሰብአዊነት በመሆኑ የዓይን ብሌንን በመለገስ የማይሻር በጎነትን መፈጸም ይገባል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ከራስ ሳይቀነስ ለሌሎች በመትረፍ የሚታወቁ የልግስና ተምሳሌትም ባለታሪካችን ናቸው። በየሦስት ወሩ ደም በመለገስ ወገንን ማዳንን የህይወት ዘይቤያቸው ያደረጉት አቶ ሞገስ በዳኔ፤ ደም ልገሳ የሰውን ህይወት ከመታደግ ባሻገር የህሊና ሰላምና ሀሴትን የሚያጎናፅፍ በጎ ተግባር መሆኑን ይመሰክራሉ።
የ19 ዓመት ወጣት ሳሉ፣ ለአንድ ጓደኛቸው እናት ደም የሚለግስ ሰው በመጥፋቱ ምክንያት ነበር ወደ ደም ባንክ ለመጀመሪያ ጊዜ ያመሩት። በዚያ አጋጣሚ የጀመሩት ይኸው ሰብአዊ ተግባር ለዓመታት ዘልቆ፣ አቶ ሞገስ እስካሁን ድረስ ለ85ኛ ጊዜ ደማቸውን ለግሰዋል።
ደም መለገስ በህይወትና በሞት መካከል ሆኖ እስትንፋሱ ሊቋረጥ የደረሰን ወገን በምድር ላይ ለማቆየት የሚደረግ ታላቅ ስጦታ ነው። ሰው በለገስነው ደም ህይወቱ ተርፎ ስናይ የሚሰማን ደስታ በምንም አይምነዘርም ይላሉ አቶ ሞገስ።
አቶ ሞገስ በየሦስት ወሩ ደም ከመለገስ ባለፈ፣ ሌላ ታላቅ የሰብአዊነት ተግባረን ለመፈጸም ወስነዋል። ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ በዓይን ባንክ ተገኝተው ቃል ገብተዋል።
በደሜና በዓይን ብሌኔ ለሰዎች የህይወት እስትንፋስንና ብርሃንን መመለስ እንደምችል ሳስበው የሚሰማኝ ደስታ ወደር የለውም ይላሉ።
ሌሎች ዜጎችም በየሦስት ወሩ ደማቸውን በመለገስ እንዲሁም በህይወት ዘመናቸው የዓይን ብሌን ልገሳ ቃል ኪዳን በመግባት ለወገኖቻቸው የህይወትና የብርሃን ምንጭ እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።