አርጀንቲና ከአልጄሪያ፣ ፈረንሳይ ከሴኔጋል – የዓለም ዋንጫው ወሳኝ ፍልሚያዎች - ኢዜአ አማርኛ
አርጀንቲና ከአልጄሪያ፣ ፈረንሳይ ከሴኔጋል – የዓለም ዋንጫው ወሳኝ ፍልሚያዎች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 9/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የስድስተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
በምድብ 10 የወቅቱ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ አርጀንቲና ከአልጄሪያ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ በካንሳስ ሲቲ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ የእግር ኳስ አፍቃሪያንን ቀልብ ስቧል።
ሁለቱ ቡድኖች በዓለም ዋንጫ መድረክ ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም እ.አ.አ በ2007 ባደረጉት ዓለም አቀፍ የወዳጅነት ጨዋታ አርጀንቲና 4 ለ 3 አሸንፋለች።
ለ19ኛ ጊዜ በዓለም ዋንጫው ተሳትፎ የምታደርገው አርጀንቲና የሶስት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ናት። የወቅቱ የዋንጫ ባለቤትም ናት።
የሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር አልጄሪያ በዓለም ዋንጫው ስትሳተፍ የአሁኑ ለአምስተኛ ጊዜ ነው።
አልጄሪያ እ.አ.አ በ2014 በብራዚል በተካሄደው 20ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ደርሳ በጀርመን 2 ለ 1 ተሸንፋ ከውድድሩ የተሰናበተችበት አጋጣሚ በውድድሩ ታሪክ ትልቁ ውጤቷ ነው።
የዘንድሮውን የዓለም ዋንጫ ያነሳሉ ተብለው ከሚጠበቁት ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው አርጀንቲና ጨዋታውን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት አግኝታለች።
ተጋጣሚዋ አልጄሪያው በጨዋታው ላይ በቀላሉ እጅ ትሰጣለች ተብሎ አይጠበቅም።
በምድብ ዘጠኝ ፈረንሳይ ከሴኔጋል ምሽት አራት ሰዓት በሜት ላይፍ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል።
ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
እ.አ.አ በ2002 ጃፓን እና ኮሪያ ሪፐብሊክ በጣምራ ባዘጋጁት 17ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ላይ ቡድኖቹ ያደጉት ጨዋታ አይረሴ የታሪክ ክስተት የተስተናገደበት ነበር።
እ.አ.አ በ1998 16ኛውን የዓለም ዋንጫ ራሷ አዘጋጅታ ሀገሯ ላይ ዋንጫውን ያስቀረችው ፈረንሳይ ጨዋታውን የማሸነፍ ሰፊ ግምት ተሰጥቷታል።
በሴኡል ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሴኔጋል በፓፓ ቡባ ዲዮፕ የ30ኛ ደቂቃ ጎል ፈረንሳይን 1 ለ 0 በማሸነፍ ዓለምን ጉድ ያስባለ ድል አስመዘገበች።
ሴኔጋል በወቅቱ እስከ ሩብ ፍጻሜ የደረሰች ሲሆን ፈረንሳይ ከምድቡ ማለፍ አለመቻሏ በወቅቱ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ከዚህ ክስተት 24 ዓመታት ቆይታ በኋላ ሀገራቱ በድጋሚ የሚገናኙበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ፈረንሳይ በዓለም ዋንጫው ለ16ተኛ ጊዜ የምትሳተፍ ሲሆን ሁለት ጊዜ ዋንጫውን አንስታለች።
በውድድሩ ላይ ለአራተኛ ጊዜ ተሳትፎዋን የምታደርገው ሴኔጋል ትልቁ ውጤቷ በ17ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ የደረሰችበት ነው።
በሌሎች መርሐ ግብሮች በምድብ 10 ኦስትሪያ ከጆርዳን ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ላይ በሳንፍራንሲስኮ ቤይ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በምድብ ዘጠኝ ኢራቅ ከኖርዌይ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ላይ በቦስተን ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።