ቀጥታ፡

የወልዲያ ከተማ የኮሪደር ልማት ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት ከመሆን ባለፈ ምቹ የመዝናኛ ሥፍራ ፈጥሯል

ደሴ፤ ሰኔ 9/2018 (ኢዜአ)፡- በወልድያ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት ከመሆን ባለፈ ምቹ የመዝናኛ ሥፍራ መፍጠሩን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

በከተማዋ እየተከናወነ ካለው 18 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ሥራ 6 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉ የሚታወቅ ነው።

የኮሪደር ልማቱን በማስመልከት ኢዜአ በወልደያ ከተማ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ የልማት ሥራው ለከተማዋ ተጨማሪ ድምቀት ከመሆን ባለፈ ምቹ የመዝናኛ ስፍራ ፈጥሮላቸዋል።   

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ጠቅል ንጉሴ የኮሪደር ልማት ሥራው ትውልድን ታሳቢ አድርጎ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፣ ለልማት ሥራው ውጤታማነት የሚጠበቅባቸውን በመወጣት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

የኮሪደር ልማቱ ለወልዲያ ከተማ ተጨማሪ ውበት ከመሆን ባለፈ ለህብረተሰቡ ምቹና አማራጭ የመዝናኛ ስፍራ እየፈጠረ መምጣቱን ገልጸዋል።


 

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ታሪኩ ሞገስ በበኩላቸው፣ በሌሎች ከተሞች በተከናወኑ የልማት ሥራዎች ቁጭት ቢፈጠርባቸውም በአሁኑ ወቅት በከተማዋ በተከናወኑ የልማት ሥራዎች መካሳቸውን ተናግረዋል።

"የዘመናት የልማት ጥያቄያችን መልስ አግኝቷል" ያሉት ነዋሪው፣ በተለይ የኮሪደር ልማቱ የወልድያ ከተማን ውበት አጉልቶ ከማውጣት ባለፈ ከተማዋን ለኑሮና ለመዝናኛነት ምቹ ማድረጉን ገልፀዋል።

በአካባቢው የሰፈነው ሰላም ለልማት ሥራ መፋጠን ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸው፣ በቀጣይም የአካባቢያቸውን ሰላም ከማጠናከር ባለፈ ለልማቱ ሲያደርጉት የነበረውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።


 

በወልዲያ ከተማ የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት ከመሆን ባለፈ ከተማዋ ለቱሪስት፣ ለኢንቨስትመንትና ለኑሮ ምቹ እንድትሆን አድርጓል ያሉት ደግሞ ሌላኛው የከተማው ነዋሪ አቶ ቸርነት እሸቴ ናቸው።

በከተማዋ ቀደም ሲል የነበረው የአስፋልት መንገድ የተበላሸና ጠባብ በመሆኑ ተሽከርካሪ፣ ሰውና እንስሳት እየተጋፉ ሲጓዙ እንደነበር አስታውሰው፣ ይህም ለትራፊክ አደጋ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል ብለዋል።

የኮሪደር ልማቱ የተሽከርካሪ፣ የብስክሌት እና የእግረኛ መንገድን ከማካተቱ ባለፈ የአረንጓዴ ልማት፣ የመዝናኛ እና የልጆች መጫወቻን ጭምር አካቶ በመከናወኑ ችግሩ መፈታቱን ገልጸዋል።

የወልድያ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ በበኩላቸው እንዳሉት፣ የከተማውን ሰላም ከማረጋገጥ ባለፈ ህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

በከተማው 18 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንና ከዚህ ውስጥ 6 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትሩ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን አመልክተዋል።

ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቃው የኮሪደር ልማት ከስታድየም-ጎንደር በር፤ ከጎንደር በር- ሙጋድ፤ ከአዳጎ አደባባይ-ሙጋድ፤ ከአዳጎ አደባባይ -ፒያሳ እና - መነኸሪያ የተከናወኑ ልማቶችን ያካተተ እንደሆንም አስረድተዋል።

ቀሪውን የኮሪደር ልማት ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ህብረተሰቡን ባሳተፈ አግባብ በርብርብ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ዱባለ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም