ቀጥታ፡

በሀገር ልማት፣ ሰላምና ብሔራዊ ጥቅምን በማስጠበቅ ረገድ የጀመርናቸውን ተግባራት አጠናክረን እንቀጥላለን - የፖለቲካ ፓርቲዎች

ሐረር፤ ሰኔ 9/2018 (ኢዜአ)፡- የሀገር ልማት፣ ሰላምና ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ተግባራትን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በሐረሪ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት አስታወቁ።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በተቋቋመበት መርህ መሠረት፣ በሀገራዊና ክልላዊ አበይት ጉዳዮች ላይ ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት በጋራ አጀንዳዎች ላይ አብሮ መስራት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው አካል ተደርጎ ይወሰዳል። 

የሐረሪ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትም በተመሳሳይ መልኩ በልማት፣ በሰላምና በብሔራዊ ጥቅም ዙሪያ የጋራ አቋም ማንጸባረቁ፣ በክልሉ ጤናማና ተቀራራቢ የፖለቲካ ባህልን ለማሳደግ እየተደረገ ስላለው ጥረት ማሳያ ነው።

ከጋራ ምክር ቤቱ አባላት መካከል የሐረሪ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ሀዲድ) ተወካይ አቶ ሁሴን ሱሌይማን እንደገለጹት፤ በፓርቲዎች መካከል የሀሳብ ልዩነቶች ቢኖሩም ለሀገርና ለክልል ልማት እንዲሁም ለሰላም በትብብር እየተከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክረው ይቀጥላሉ።

በተለይም የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ዘላቂ ምላሽ እንዲያገኝ በሚደረገው ጥረትና በሌሎችም ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ዙሪያ የማይደራደሩ መሆናቸውን አቶ ሁሴን አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

የሀገርን ሰላም ለማወክና ብሔራዊ ጥቅምን ለማሳጣት ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ አካላትን አፍራሽ ተግባር ፓርቲያቸው በንቃት እየተከታተለ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሁሴን፤ እነዚህን ኃይሎች ከህዝብ ጋር በመተባበር በቁርጠኝነት እንደሚታገሏቸውም አስታውቀዋል።

የሐረሪ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ተወካይ ሀሰነት ሙሜ በበኩላቸው፤ ፓርቲው የኢትዮጵያን ልማት፣ ሰላምና ብሔራዊ ጥቅምን አስቀድሞ የሚሄድና ለሀገር  አፍራሽ የሆኑ ተግባራትን የሚታገል  ነው።

"ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት ያለ ልዩነት በቅንጅት እንሰራለን"  ያሉት ወይዘሮ ሃሰነት፤ በተለይም ለሀገር ጠንቅ የሆኑ የጽንፈኞችን ተግባር የጋራ ምክር ቤቱ በንቃት እየተከታተለና በአቋም ደረጃ የሚታገል መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በመሰባሰብና በመወያየት በክልሉ  ዘላቂ ልማት፣ ሰላምና ሁለተናዊ እድገት ላይ ፓርቲያቸው በቅንጅት እየሰራ ነው ያሉት ደግሞ የጋራ ምክር ቤቱ አባልና የኢዜማ ተወካይ ማህሌት ዘውዱ ናቸው።

ሀገርን ለማተራመስና ብሔራዊ ጥቅምን ለማሳጣት የሚሞክሩ ሃይሎች ከባለፈው ክስተት ያልተማሩና ለህዝብ የማያስቡ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ከዚህ ድርጊት እንዲታቀቡና በጠረጴዛ ዙሪያ በመነጋገር ለህዝብ ጥቅም መረጋገጥ ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

በክልሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ በተለያዩ የልማት መስኮችና የሀገርን ጥቅም በሚያስከብሩ ተግባራት ላይ የፖለቲካ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው በጋራ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዳይሬክተር አቶ ሀሰን አብዲ ናቸው።

የክልሉን  ልማትና ሰላም በማጽናት ሀገሪቱን ወደፊት የማስኬድ ተግባርን  አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አክለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም