ቀጥታ፡

በባሌ ዞን ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ዝግጅት እየተደረገ ነው

ሮቤ፤ ሰኔ 9/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል።


 

ዘንድሮ የተያዘውን የ8 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል ግብ ለማሳካት በሚደረገው ብሔራዊ የንቅናቄ ሥራ ላይ በሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለተግባራዊነቱ እንዲረባረቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጥሪ ማቅረባቸውም ይታወሳል።

በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ስኬታማ ለማድረግ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ሥራ እየተሠራ ይገኛል።


 

የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሙአዊያ ፉአድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ ባለፉት ዓመታት ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በተከናወነው መርሃ ግብር የተራቆተ መሬትን መልሶ በደን በመሸፈን ረገድ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል።

ይህንን ተግባር ለማስቀጠልም በመጪው ክረምት የሚተከሉ ከ229 ሚሊዮን የሚበልጡ ችግኞችን በመንግስት፣ በማህበራትና በግል የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች የማዘጋጀቱ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

እስካሁን ከ211 ሚሊዮን በላይ ችግኞች የተዘጋጁ ሲሆን፣ 194 ሚሊዮን የሚሆኑ የመትከያ ጉድጓዶች መዘጋጀታቸውንና ቀሪው ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዞኑ በችግኝ ማፍያ ጣቢያዎቹ በአብዛኛው ሀገር በቀልና ሌሎች የውጭ ዝርያ ችግኞች መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ በጽህፈት ቤቱ የተፋሰስና የደን ልማት ቡድን መሪ አቶ ተስፋዬ ኦሊቃ ናቸው።


 

አካባቢው በዓመት ሁለት ጊዜ የበልግና የክረምት ዝናብ የሚያገኝ በመሆኑ ተከላውም ይህንን ስነ-ምህዳር ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ከመጋቢት መጀመሪያ እስከ ሚያዝያ መጨረሻ በጣለው የበልግ ዝናብ 105 ሚሊዮን የሚሆኑ ችግኞች መተከላቸውንና ቀሪው ተከላ በሐምሌ ወር እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ከተዘጋጁት ችግኞች መካከል ጥድ፣ ኮሶ፣ ዋንዛ፣ ዝግባ፣ ግራቪሊያ፣ የእንስሳት መኖና የጥላ ዛፎች የሚገኙበት ሲሆን፣ 8 በመቶ ያህሉ ደግሞ ለሰው ምግብነት የሚውሉ አትክልትና ፍራፍሬ ናቸው ብለዋል።


 

የሐረና ቡሉቅ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኢብራሂም ሐሰን፤ በወረዳው የህዝቡን የድርቅ ተጋላጭነት ለመከላከል የተጀመረው ጥረት ህብረተሰቡን በማሳተፍ መጠናከሩን ገልጸዋል።

በዚህም በ60 በመቶው የበልግ ዝናብ በመጠቀም፣ ለተከላ ከተዘጋጁ 25 ሚሊዮን ችግኞች መካከል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነውን መትከል መቻሉን አስታውቀዋል።

ከወረዳው ነዋሪዎች መካከል አርብቶ አደር ጀማል ሁሴን በሰጡት አስተያየት፤ የድርቅ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ችግኝ መትከል የህልውና ጉዳይ መሆኑን ካለፉት ዓመታት ተጨባጭ ውጤት መረዳታቸውንና በዘንድሮው መርሃ ግብር ላይ በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል።

በባሌ ዞን ባለፈው የክረምት ወቅት ከተተከሉ ከ245 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መካከል በተደረገ ቆጠራ 87 በመቶው ጸድቆ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም