የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቀን ከ250 ሲሊንደር በላይ የሕክምና ኦክስጅን በማምረት ከራሱ አልፎ ለአካባቢ የህክምና ተቋማት ማቅረብ ጀምሯል - ኢዜአ አማርኛ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቀን ከ250 ሲሊንደር በላይ የሕክምና ኦክስጅን በማምረት ከራሱ አልፎ ለአካባቢ የህክምና ተቋማት ማቅረብ ጀምሯል
አዲስ አበባ፤ሰኔ 9/2018(ኢዜአ)፦የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቀን ከ250 ሲሊንደር በላይ የሕክምና ኦክስጅን በማምረት ከራሱ አልፎ ለአካባቢ የህክምና ተቋማት ማቅረብ መጀመሩን ገለጸ፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተመሰረተበትን 70ኛ ዓመትና የማስተማሪያ ሆስፒታሉን 100ኛ ዓመት ባለፈው ዓመት ማክበሩ ይታወሳል፡፡
በዚህም ዩኒቨርሲቲው የተቋቋመበትን የማህበረሰቡን ችግር ፈች አገልግሎት የመስጠት ዓላማ ታሳቢ በማድረግ ከ20 በላይ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን አስመርቋል፡፡
የጨረር ሕክምና ማዕከል፣ የሕክምና ኦክስጅን ማምረቻ፣ ዘመናዊ የደረቅና እርጥብ ቆሻሻ ማስወገጃና ሌሎችም ማህበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክቶች በምርምር ተቋቁመው ገቢራዊ ተደርገዋል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምህንድሥና ሥራ አገልግሎት ዳይሬክተር እና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ኢንጂነር ወንደወሰን በየነ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የዩኒቨርሲቲው ሆስፒታል ታካሚዎች ሕክምና የሚያገኙት ከአዲስ አበባ ተገዝቶ በሚመጣ የሕክምና ኦክስጅን ነበር፡፡
በአሁኑ ወቅት ማዕከሉ በቀን 250 ሲሊንደር እና ለ600 የህሙማን አልጋዎች በቀጥታ የሚደርስ የሕክምና ኦክስጅን በማምረት እጥረቱን ሙሉ በሙሉ መፍታት ችሏል ብለዋል፡፡
የሕክምና ኦክስጅን ማዕከሉ ኦክስጅን ለማምረትየተፈጥሮን አየርን በማጣራት ጥቅም ላይ እንደሚያውል ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከራሱ አልፎ ለአካባቢው የሕክምና ተቋማት የሕክምና ኦክስጅን እያቀረበ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ አድማሱን በማስፋት ምርቱን የማሳደግና ገቢ የማመንጨት እቅድ ይዟል ብለዋል፡፡