የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ዲጅታል ከማድረግ ባለፈ በብቁ ባለሙያዎች አገልግሎት እንዲሰጥ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ዲጅታል ከማድረግ ባለፈ በብቁ ባለሙያዎች አገልግሎት እንዲሰጥ እየተደረገ ነው
ባህር ዳር፤ ሰኔ 9/2018 (ኢዜአ) ፡-የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ዲጅታል ከማድረግ ባለፈ በእውቀትና ክህሎት በብቁ ባለሙያዎች የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ እየተደረገ መሆኑን የአማራ ክልል የሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ገለጸ።
በክልሉ የሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ የሪፎርም ድጋፍና ክትትል ዳይሬክተር አቶ እንዳላማው ይታይህ፤ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙ በአገልግሎት አሰጣጥና ተቋማት ውጤታማ እንዲሆኑ ከማድረግ አንፃር ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግቧል ብለዋል።
በሪፎርሙ የሰራተኛው የመፈፀም አቅም፣ ነፃና ገለልተኛ ተቋም በመፍጠርና ፈጣን አገልግሎት በመስጠት ረገድ እመርታ የተመዘገበበት መሆኑን ተናግረዋል።
የመንግስትን አገልግሎት አሰጣጥ ዲጅታላይዝ በማድረግ ሂደት ሰራተኛውን ለላቀ አፈፃፀም በማብቃትም ብዙ ስኬቶች ተገኝተዋል ብለዋል።
በመሆኑም የአገልግሎት አሰጣጥን ዲጅታል ከማድረግ ባለፈ በእውቀትና ክህሎት በብቁ ባለሙያዎች የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉ ገንዘብ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ደሳለኝ አለምነህ፤ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርምን በመተግበር የሚጨበጥ ውጤት ስለመታየቱ ተናግረዋል።
የሰራተኛውን የስራ ባህል በመቀየር ቀልጣፋ፣ ዘመናዊና በዲጅታል አሰራር የታገዘ አገልገሎት እየተሰጠ መሆኑን አንስተዋል።
የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አባይ መንግስቴ፤ በተቋማት የሚስተዋሉ የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የተጀመረው ጥረት በውጤታማነት መቀጠሉን ገልጸዋል።
የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ ከዘመኑ ጋር የሚራመድ የዲጅታል አገልግሎት እየተስፋፋ በመምጣቱና ለዚህ ብቁና ዝግጁ የሆነ የሰው ሃይል ማፍራት መቻሉ ለስኬቱ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።