ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሕክምና ቱሪዝም መዳረሻ የሚያደርጋትን መሠረት እየገነባች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሕክምና ቱሪዝም መዳረሻ የሚያደርጋትን መሠረት እየገነባች ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 9/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት የሕክምና ቱሪዝም ማዕከል የሚያደርጋትን መሠረት እየገነባች መሆኑን የኢትዮጵያና የምሥራቅ አፍሪካ ጤና ክብካቤ ፌዴሬሽኖች ፕሬዝዳንት ዶክተር ማርቆስ ፈለቀ ገለጹ።
የኢትዮጵያና ምሥራቅ አፍሪካ ጤና ክብካቤ ፌዴሬሽኖች ፕሬዝዳንት ዶክተር ማርቆስ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የሕክምና ቱሪዝም ማዕከል መሆን የሚያስችል አቅም ቢኖራትም በአግባቡ ጥቅም ላይ ሳይውል ቆይቷል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ዜጎች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት በማሟላት ኢትዮጵያን የሕክምና ቱሪዝም ማዕከል ማድረግ የሚያስችል ሥራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መንግስት የዲጂታል የጤና ስርዓት በመዘርጋት በብቁ የሕክምና ባለሙያዎች የተሟሉ የሕክምና ተቋማት እየገነባ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያን የሕክምና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የሕክምና አገልግሎት መሣሪያዎችና የሕክምና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት፡፡
የወራቤ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሊድ ሸረፋ፤ ኢትዮጵያን የሕክምና ቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ ለሕክምና ወደ ውጭ የሚሄዱ ዜጎችን የሚያውጡትን የውጭ ምንዛሪ ከማስቀረት ባለፈ ለሕክምና ወደ ኢትዮጵያ ከሚመጡ ዜጎች ተጨማሪ ገቢ ማግኘት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡
መንግስት የሕክምና ቱሪዝምን ለማሳደግ የሕክምና መሠረተ ልማቶችን እያስፋፋ መሆኑን ገልጸው፤ ጥራት፣ ደህንነትና ተደራሽነትን መሠረት ያደረገ አገልግሎት በመስጠት ሚናቸውን እንደሚወጡም ጠቁመዋል፡፡
የመቅረዝ ጠቅላላ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ናትናኤል ታዬ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያን የሕክምና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
መንግሥት ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የጀመራቸው ሥራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጸው፤ የጤና ተቋማትን ማዘመንና በሀገር ውስጥ የሌሉ ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎች በስፋት እንዲገቡ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አንስተዋል፡፡
መንግስት የሕክምና መድኃኒቶችና ግብዓቶች በሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ለማጠናከር ለፋርማሲዩቲካል ዘርፉ ትኩረት በመስጠት የሕክምና ተቋማት በወቅቱና በዓይነት እንዲደርሳቸው ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም አድንቀዋል፡፡