ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 35ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 9/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ35ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና መቀሌ 70 እንደርታን ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ያገናኛል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ46 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው መቀሌ 70 እንደርታ በ35 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻለው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የአሸናፊነትን መንገድ ለማግኘት ይጫወታል።

ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ሶስት ነጥብ ያገኘው መቀሌ 70 እንደርታ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚያደርገው ትግል የዛሬውን መርሐ ግብር በድል መወጣት ይኖርበታል።

በሌላኛው መርሐ ግብር ባህር ዳር ከተማ ከወላይታ ድቻ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች አቻ የተለያየው ባህር ዳር ከተማ በ46 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል።

ባህር ዳር ከተማ በውድድር ዓመቱ በርካታ ጨዋታዎች አቻ የወጣ (19 ጊዜ) ቡድን ነው።

ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች አቻ የተለያየው ወላይታ ድቻ በ44 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ወላይታ ድቻ ከባህር ዳር ከተማ በመቀጠል በሊጉ በርካታ ጨዋታዎች አቻ የተለያየ (17 ጊዜ) ቡድን ነው።

ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታሉ።

ሸገር ከተማ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከቀኑ 9 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በ34ኛ ሳምንት ፋሲል ከነማን 1 ለ 0 የረታው ሸገር ከተማ በ43 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ተጋጣሚው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ በ41 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል።

ጨዋታው ሸገር ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም