የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሐቆች - ኢዜአ አማርኛ
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሐቆች
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን ጥር 2 ቀን 2018 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስጀምረውታል።
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ከባሕር ጠለል በላይ በ1 ሺህ 910 ሜትር ከፍታ ላይ እየተገነባ ይገኛል።
በዓመት እስከ 110 ሚሊየን መንገደኞችን የማስተናገድ ዐቅም አለው።
አሁን ካለው የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የማስተናገድ ዐቅም ጋር ሲነጻጸር በ4 ነጥብ 4 እጥፍ ብልጫ ይኖረዋል።
ይህ ታሪካዊ ፕሮጀክት፣ ሀገራችንን ከዓለም ቀዳሚ የአቪዬሽን ማዕከላት ተርታ ለማሰለፍ ሌሊትና ቀን በከፍተኛ ጥረት እየተገነባ ይገኛል።
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአፍሪካ ታሪክ ትልቁ የአቪዬሽን መሠረተ-ልማት ፕሮጀክት ነው።
የአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታው የሚከናወነው በሁለት ምዕራፍ ነው።
የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ 60 ሚሊየን መንገደኞች የማስተናገድ ዐቅም በመያዝ እንደ አውሮውፓውያን አቆጣጠር በ2030 እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።
በዚህ ምዕራፍ አንድ እጅግ ትልቅና ዘመናዊ እንዲሁም አንድ መለስተኛ የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናሎች ይገነባሉ።
በተጨማሪም በመጀመሪያው ምዕራፍ ሁለት በተጓዳኝ የሚሠሩ የአውሮፕላን መንደርደሪያዎች እንዲሁም 180 አውሮፕላኖችን በአንድ ጊዜ ማቆም የሚያስችል ቦታ ይገነባል።
በዚሁ ምዕራፍ 350 ማረፊያ ክፍሎች ያሉት ዘመናዊ ሆቴል በተርሚናሉ ውስጥ ይገነባል።
በዓመት 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ቶን ጭነት የሚያስተናግድ የካርጎ ተርሚናል እና የአውሮፕላን ጥገና ማዕከልም በዚሁ ምዕራፍ የሚገነባ ይሆናል።
ፕሮጀክቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ አህጉርም ትልቅ አርአያ ነው።
የአፍሪካ ነፃ አኅጉራዊ ንግድ ቀጣናን ተግባራዊነት ለማቀላጠፍና የአኅጉሪቱን የንግድና የኢኮኖሚ ትስስር ለማጠናከር ቁልፍ ሚና ይጫወታል።
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጋር የሚያገናኝና በአንድ ጊዜ 12 ተሽከርካሪ ማስተናገድ የሚችል የፍጥነት መንገድ እንዲሁም ፈጣን የባቡር መንገድ ይገነባል።
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የአፍሪካን አቪዬሽን እድገት አስሮ የያዘውን የመሠረተ-ልማት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የተወሰደ ትልቅ እርምጃ ነው።
ይህ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ፕሮጀክት ከፍተኛ የሥራ ዕድል ይፈጥራል።
ከአውሮፕላን ማረፊያው ጋር ተያይዞ የሚመሠረተው የኤርፖርት ከተማም በንግድ፣ በኢንዱስትሪና በቱሪዝም ዘርፎች ለአካባቢው ዕድገት ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል።