ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለከተማዋ አካባቢ ጥበቃ፣ ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 9/2018(ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለአጋሮ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ፣ ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር ገለጸ።

የከተማዋ ወጣቶችም በአረንጓዴ አሻራ ሥራ ላይ በማህበር ተደራጅተው በመስራታቸው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ከማሳደጋቸው ባለፈ ለሌሎች ሰዎችም የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኞችን በማፍላትና በመትከል እንዲሁም በመንከባከብ የጽድቀት መጠናቸውን በማሳደግ ካላቸው ሁሉ አቀፍ ጥቅም በተጨማሪ ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ ይጠበቃል።


 

በመሆኑም ህብረተሰቡ ልክ እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ ዘንድሮም በችግኝ ተከላው ተሳትፎውን በማጠናከር አረንጓዴ፣ ጤናማ እና ዘላቂ ሕይወት ያለው አካባቢ ለመፍጠር መሥራት ይገባዋል።

የአጋሮ ከተማ ነዋሪዎች ቀደም ባሉት ጊዜያት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የችግኝ ተከላ ሥራው ላይ በንቃት በመሳተፋቸው ተጠቃሚነታቸው ማደጉ ተመላክቷል።

ዘንድሮ በሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይም በንቃት እና በተደራጀ አግባብ በመሳተፍ ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚሰሩ ተገልጿል።

የአጋሮ ከተማ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እንዳለ ማመጫ እንደገለጹት፣ በከተማዋ ባለፉት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ገብር ላይ ህብረተሰቡን በስፋት በማሳተፍ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።

በዚህም ለከተማዋ አካባቢ ጥበቃ፣ ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በዚህም ህብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ መሆኑ በተጨባጭ መታየቱን ጨምረው ተናግረዋል።

በዘር ዝግጅት፣ ችግኝ በማፍላት፣ በመጓጓዣ፣ በተከላ፣ በደን እንክብካቤ እና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፎች ላይ ለበርካታ ሰዎች የአጭርና የረጅም ጊዜ የሥራ ዕድሎች መፍጠር መቻሉንም አክለዋል።

ዘንድሮ ለሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ የተለያዩ ዝርያዎች ያላቸው ችግኞች ዝግጅት መከናወኑንም ጠቁመዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ከመገንባትና አካባቢን ከማስዋብ ባሻገር የሥራ ዕድል በመፍጠር የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና እንዳለውም በሥራው ላይ የተሳተፉ የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በዘርፉ ተሰማርተው ውጤታማ ከሆኑ ወጣቶች መካከል ፈሪድ ነዚፍ እንደተናገረው፣ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ በማህበር ተደራጅተን በመስራታችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችን ከማደጉ ባለፈ ለሌሎች ሰዎችም የሥራ ዕድል መፍጠር ችለናል ብሏል።

ወጣት ኑሬ አባ ጀባል በበኩሉ፣ በማህበር ተደራጅተው በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሚሰሩት የ"grafting" (የተክል ማጣመር) ሥራን በመሥራትና በመሸጥ ቤተሰባችንን እያስተዳደርን እንገኛለን ሲል ገልጿል።

ሌላኛው ወጣት ምርጋኒ አባ ፊጣ በበኩሉ፣ በማህበር ተደራጅተን በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ ችግኞች ዝግጅት ላይ በመሳተፍ ተጠቃሚነታችን እያደገ ነው ብሏል።

በአረንጓዴ አሻራ ዘርፍ ላይ በምንሰራው ስራ ሁሉ የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ አልተለየንም ያለው ወጣት ምርጋኒ ለወጣቶችና ለሴቶች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ገቢያቸው እንዲሻሻል እያደረገ ይገኛል ሲል ተናግሯል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም