ቀጥታ፡

አረንጓዴ ዐሻራ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትና ብልፅግና አሰናስሎ የሚያረጋግጥ ወሳኝ የልማት አቅጣጫ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 8/2018(ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትና ብልፅግና አሰናስሎ የሚያረጋግጥ ብሔራዊ የልማት አቅጣጫ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ኢትዮጵያ ኮፕ-32ን ስታስተናግድ 65 ቢሊየን ችግኞችን መትከል የቻለች ሀገር መሆኗን ለዓለም እናበስራለንም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሀሳብ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ሐይቅ ዳርቻ አስጀምረዋል።


 

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የዘንድሮው አረንጓዴ ዐሻራ ማስጀመሪያ በቢሾፍቱ ከተማ መካሄዱ ከተማዋ ከራሷ አልፎ ለአዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች ችግኞችን የምታመርት መሆኗን ዕውቅና የሚሰጥ ነው።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትና ብልፅግና አሰናስሎ የሚያረጋግጥ ብሔራዊ ኢኒሼቲቭ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የደን፣ የሰብልና ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት የማረጋገጥ ወሳኝ የልማት አቅጣጫ መሆኑን አስረድተዋል።


 

የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት የሚደፈረው በሁለት ጉዳዮች ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አንዱ ባዕዳን ኃይሎች አልመውና ድንበር ጥሰው ሲገቡ ሲሆን፤ ሌላኛው የእኛ ሃብትና ንብረት በዋዛና ፈዛዛ ሲወጣም የሉዓላዊነት መደፈር ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያም ባለፉት ዓመታት ያጣችው የአፈር መጠን በገንዘብ ሊተመን የማይችል ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል።

የእኛ አባቶች ዓድዋ ላይ ወራሪን በማሳፈር ገድል ሠርተዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ የእኛ ትውልድም በአረንጓዴ ዐሻራ ሌላኛውን ለትውልድ የሚሻገር ታላቅ ገድል እየሰራ ነው ብለዋል።

የዘንድሮው "ተስፋን እንትከል" መሪ ሃሳብ የነገን ብሩህ ዛሬ በመፃፍ፣ የተስፋ ስሮች ዘልቀው የብልፅግና ግንድ፣ ቅርንጫፍና ፍሬ ተስፋፍቶ ሃብት እንዲሆኑ የሚያመላክት መሆኑንም ተናግረዋል።

የተስፋ ምርጫም የቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪዎችና መላው ኢትዮጵያውያን በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የትኛውም የአየር ሁኔታ ሳይበግራቸው ተስፋን በመሰነቅ ድምፅ መስጠታቸውን ከመሪ ሃሳቡ ጋር አሰናስለው አስገንዝበዋል።


 

ተስፋ የአረንጓዴ መቀነት ነው፣ ሀገርን ያለብሳል፣ የተራቆተና የገረጣን መሬትም ያለመልማል፣ ተስፋ አረንጓዴ ፀዳልና መንፈስን የሚያድስ አረንጓዴ ወርቅ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የአረንጓዴ ውርስ ትውልድ የሚከበርበት ቀጣዩ ትውልድ ልምድና ባህል የሚያደርገው የብልፅግና መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ በመደመር መርህ የኢትዮጵያን የተረጂነት ታሪክ ወደ ማድረግ ዘመን የሚያሸጋግር መሆኑን አንስተው፤ መርሃ ግብሩ አፈራችንን ከስደት፥ ግድባችንን ከደለል የሚታደግ ስኬታማ የልማት ዓምድ ነው ብለዋል።

ከአስር በላይ አዳዲስ የፍራፍሬ ዝርያዎችን በኢትዮጵያ በማላመድ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችል ስራ እየተሰራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ለዚህ ስኬትም ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ በችግኝ ማፍላት፣ በእንክብካቤ፣ በመትከል፣ በችግኝ ሽያጭ፣ በንብ ማነብና በእንስሳት ማድለብ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን አብራርተዋል።

በቀጣይም የበለፀገች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ በሁሉም መስክ የተመዘገበውን ስኬት ማስፋትና ማስቀጠል እንደሚያስፈልግም አፅንኦት ሰጥተዋል።

ከ2011 ዓም ጀምሮ በተከናወነ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ48 ቢሊየን በላይ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን ጠቁመው፥ ዘንድሮም ከስምንት ቢሊየን በላይ ችግኝ በመትከል በአጠቃላይ 56 ቢሊየን እንደሚደርስ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ኮፕ-32ን ስታስተናግድ 65 ቢሊየን ችግኞችን መትከል የቻለች ሀገር መሆኗን ለዓለም እናበስራለን ብለዋል።

ለዚህም ሁሉም ዜጋ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዐሻራ ስኬት በማስቀጠል በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በሚቀጥሉት የክረምት ወራትም "ተስፋን በመትከል" በዓድዋ ድል ቅድመ አያቶች የተቀዳጁትን ድል በአረንጓዴ አሻራ ልማት በመድገም የኩራት ምንጭ የሆነች ኢትዮጵያን ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም