ቀጥታ፡

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር 11 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት በደን መሸፈን አስችሏል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 8/2018(ኢዜአ)፦ ባለፉት ሰባት ዓመታት የተከናወነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር 11 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት በደን እንዲሸፈን ማስቻሉን የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ዛሬ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ሐይቅ ዳርቻ በይፋ አስጀምረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት በዚህ ዓመት 8 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ግብ በማስቀመጥ ከፍ ወደ አደረግነው 65 ቢሊየን ችግኞች ግብ የመድረስ ትልማችንን ለማሳካት በጽናት እየገሰገስን እንገኛለን ብለዋል።

የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ እንዳሉት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር መንግሥትና ሕዝብ ተቀናጅተው ያሳኩት ታላቅ ታሪክ ነው።

ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት ሰባት ዓመታት 48 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸውን አንስተው በየዓመቱ በአማካይ 25 ሚሊየን ዜጎች በመርሃ ግብሩ መሳተፋቸውንም ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ ከተተከሉት ችግኞች መካከል 60 በመቶ ያህሉ ለጥምር እርሻ የሚውሉ መሆናቸውን አንስተው 35 በመቶ ያህሉ ደግሞ የደን ዛፎች ናቸው ብለዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ትግበራ 11 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት በደን እንዲሸፈን ማስቻሉንም አስረድተዋል።

የሀገሪቱን የደን ሽፋን ከማሳደጉ ባለፈ የአረንጓዴነት ምጣኔን በመጨመር ወደ ውሃ አካላት የሚወርደውን የደለል መጠን እንዲቀንስ አስችሏል ነው ያሉት።

የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ በየዓመቱ ወደ ወንዞች ታጥቦ ይገባ የነበረውን የአፈር ሀብት ከ2 ቢሊየን ቶን ወደ 208 ሚሊየን ቶን ዝቅ እንዲል ማስቻሉን ተናግረዋል።

መርሃ ግብሩ የአፈር ለምነትን በመጨመር ምርታማነትን ማሳደግ ማስቻሉን አንስተው የመድረቅ አደጋ ተጋርጦባቸው የነበሩ የውሃ አካላት እንዲያገግሙ አድርጓልም ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሚያስችል አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባትም ትልቅ አቅም እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም