ቀጥታ፡

ረቂቅ አዋጁ ዘመናዊ የታክስ ሥርዓት ለመዘርጋት ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል - ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 8/2018(ኢዜአ)፦ የፌዴራል ታክስ አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ዘመናዊ የታክስ ሥርዓት ለመዘርጋት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

በምክር ቤቱ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ታክስ አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ የሕዝብ ይፋዊ ውይይት መድረክ አካሂዷል።

በገንዘብ ሚኒስቴር የሕግ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ተወዳጅ መሀመድ የማሻሻያ አዋጁን መነሻ ሃሳብ ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት አዋጁ የታክስ አስተዳደሩን ቀልጣፋ በማድረግ የሀገርን ኢኮኖሚ ማሳደግ የሚያስችል ነው።


 

የግብር ከፋዮችን መብትና ግዴታ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ በማስከበር ፍትሐዊነትንና ታክስ የመክፈል ግዴታን በተጠናከረ መልኩ ማስፈፀም እንደሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም ታክስ ከፋዩ በታክስ ሥርዓቱ አመኔታ ኖሮት ግዴታውን በአግባቡ እንዲወጣ እንደሚረዳ ገልፀዋል።

የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሀብረቢ የታክስ አስተዳደር አዋጁ ማሻሻያ የተቀላጠፈ ሥርዓት በመገንባት ከግብር ከፋዩ የሚነሱ ቅሬታዎችን ምላሽ መስጠት የሚያስችል እንደሆነ አስታውቀዋል።

ታክስን በአግባቡ በመሰብሰብ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ በውስጥ አቅም መሸፈን የሚያስችል ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብለዋል።


 

ከሰው ንክኪ ነፃ የሆነ በዲጂታል የተደገፈ አሠራር በመዘርጋት ተደራሽነትና ቅልጥፍናን በማረጋገጥ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱን ከብልሹ አሠራር ነፃ እንዲሆን ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጆ በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ በታክስ ሥርዓቱ ላይ ተግዳሮት የሆኑ ጉዳዮችን ለማረም መዘጋጀቱን አንስተዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰበሰበው የታክስ ገቢ እያደገ ነው ያሉት ሰብሳቢው ይህም የማክሮ ኢኮኖሚ፣ የፊሲካል ፖሊሲና የታክስ ሥርዓት ማሻሻያዎችን ውጤታማነት የሚያሳይ መሆኑን ገልፀዋል።

በግብር ከፋዩ ዘንድ እየተሠራ ያለው የግንዛቤ ፈጠራ እና ማበረታቻ የግብር ከፋዮችን ተነሳሽነት በማሳደግ ግዴታቸውን እንዲወጡ እያስቻለ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም