ቀጥታ፡

በዓለም ዋንጫው አፍሪካዊቷ ኬፕቨርዴ ከስፔን ጋር አቻ ተለያየች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 8/2018 (ኢዜአ):- በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የምድብ ስምንት የመጀመሪያ መርሐ ግብር ስፔን እና ኬፕቨርዴ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ማምሻውን በአትላንታ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ስፔን በኳስ ቁጥጥር እና በግብ ሙከራ ከፍተኛ ብልጫ ብትወስድም ጎል ከመረብ ላይ ማሳረፍ ተስኗታል።

በአንጻሩ ኬፕቨርዴ በጨዋታው ላይ የተከተለቸው የመከላከል ስልት አንድ ነጥብ አስገኝቶላታል።

የኬፕቨርዴው ግብ ጠባቂ ቮዚኒሃ ያዳናቸው ኳሶች ወሳኝ ነበሩ።

166 ሺህ ህዝብ ያላት የአፍሪካ የደሴት ሀገር ኬፕቨርዴ ከእግር ኳስ ኃያሏ ስፔን ነጥብ በመውሰድ ያልተጠበቀ ውጤት አስመዝግባለች። ብሔራዊ ቡድኑ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ እየተሳተፈ ይገኛል።


የአንድ ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ስፔን ጉዞዋን በአቻ ውጤት ጀምራለች።

በዚሁ ምድብ ሳዑዲ አረቢያ ከኡሯጓይ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ላይ በሚያሚ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም